አቶ ኤርሚያስ አመልጋ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ከእስር እንዲለቀቁ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ወሰነ

ኢሳት (መጋቢት 15 ፥ 2015)

የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከሁለት ወር በፊት የገቡትን ቃል አልፈጸሙም ተብለው ለእስር የተዳረጉት የአክሰስ ሪል ስቴት መስራችና ባለቤት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ከእስር እንዲለቀቁ ሃሙስ ወሰነ።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን በግማሽ ሚሊዮን ብር ዋስትና ከእስር ቤት እንዲወጡ ቢወስንም ከሃገር እንዳይወጡ ግን እገዳ ማስቀመጡን ከሃገር በት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

በአቶ ኤርሚያስ ላይ ምርመራን እያካሄደ የሚገኘው መርማሪ ቡድን በበኩሉ የግማሽ ሚሊዮን ብር ዋስትናው በቂ አይደለም በማለት ተቃውሞ ቢቀርብም ችሎቱ የቀረበው ተቃውሞ ሶስተኛ ወሩን በያዘው የምርመራ ሂደት ላይ አጥጋቢ አይደለም ሲል ውድቅ ማድረጉ ታውቋል።

አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ላለፉት ሶስት አመታት ምንም አይነት ገቢ አለማግኘታቸውን እና ቤተሰቦቻቸው ድጋፍ ብቻ ህይወታቸውን እየመሩ እንደሆነ ለችሎት አስረድተዋል።

ከሶስት ወር በፊት ከውጭ ሃገር ከመንግስት የተሰጣቸው ያለመከሰስ ዋስትና ተጠቅመው ወደ አዲስ አበባ የተመለሱ አቶ ኤርሚያስ የገቡትን ቃል አልፈጸሙም በሚል በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል።

25 ሺ ብር ብቻ እንዳላቸው ለችሎት የተናገሩት አቶ ኤርሚያስ የተጠየቁትን ግማሽ ሚሊዮን ብር ዋስትና ማስያዝ ከቻሉ በቀጥዩ ቀናት ከእስር ቤት ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

2 ሺ 500 የሚሆኑ ቤት ፈላጊዎች ቅድመ ክፍያን ብንከፍልም አክሰስ ሪል ስቴት ኩባንያ ቤት ሊያስረክበን አልቻለም በማለት ቅሬታን ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

ከኩባንያው የሽርክና ድርሻ ያላቸው ቤት ፈላጊዎች ያቀረቡት ቅሬታ ተከትሎም አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ሲዘገብ ቆይቷል።

የአቶ ኤርሚያስ ጠበቆች በበኩላቸው መንግስት የገባውን ቃል በመጣስ ደንበኛቸው ያለአግባብና ከህግ ውጭ አስሯል በማለት አቶ ኤርሚያስ የዋስ መብታቸው ተጠብቆ ከእስር እንዲለቀቁ ሲጠየቁ መቆየታቸውንም ለመረዳት ተችሏል።