(ኢሳት ዲሲ–ጥር 4/2010)
አቶ አዲሱ ለገሰ በቅማንት ጉዳይ ላይ የጀመሩትን ሕዝብን የመከፋፈል ሴራ መቀጠላቸው ተነገረ ።
የሕወሃትን ጉዳይ በማስፈጸም የሚታወቁት አቶ አዲሱ ለገሰ በጎንደር በተገኙበት ስብሰባ በብአዴን አባላት ሳይቀር ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።
ሕዝቡም ቁጣውን በመግለፅ አቶ አዲሱ የተገኙበትን ስብሰባ ረግጦ ወጥቷል ፡፡
አቶ አዲሱ ለገሰ ጥር 2/2010 ምሽት በነበረው በረራ ጎንደር በመግባት “የቅማንት ኮሚቴ ” ነን በማለት በህወሃት የተቋቋሙ ግለሰቦችን አነጋግረዋል።
በዚህ ወቅት እነዚህ ኮሚቴዎች በብአዴን በኩል እየቀረበ ያለውን የሀብት ክፍፍል፣አይከል ከተማን በተመለከተ ግማሹ ቀበሌ የአማራ ነው የሚባለውን ሀሳብ እንደሚቃወሙ ነግረዋቸዋል።
አመራሮችን በመሾም በኩል ብአዴን ለእኛ ሊሾምልን አይገባም፣ብአዴን የኛ ጠላት ነው፣ ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችና ሀሳቦች ቀርበው እንደነበረም ነው የተገለጸው።
አቶ አዲሱ ለገሰም ይህን ሀሳብ በመያዝ እና ጉዳዩን ለማስፈፀም ወደ ህዝብ ሲገባ በብአዴን አባላት ሳይቀር ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል።
በወቅቱ ከ11 ቀበሌዎች የተመረጡ ነዋሪዎች ሳይቀር አቶ አዲሱ የተገኙበትን ስብሰባ ረግጠው ወጥተዋል ነው የተባለው ፡፡
ጥር 3/2010 በነበረው ጊዜም አድርባዬችን በመምረጥ ስብሰባው ለዛሬ መቀጠሩም ታወቋል።
በስብሰባው ዋና ተዋናይ የሆኑት አቶ አዲሱ ለገሰ፣ አቶ ሙሌ ታረቀኝ፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣አቶ አለምነው መኮነን እንዲሁም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አመራሮችና የመከላከያ አመራሮች ናቸው።
በአሁኑ ጊዜ የህዝቦች መተባበር፣ መፈቃቀር ብሎም ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ እየወጣ መምጣቱ ህወሓትንና ጉዳይ አስፈጻሚዎቹን እጅግ እያስደነገጣቸው ይገኛል ፡፡