አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር እንዲፈታ የሚጠይቅ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ተጀመረ

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር እንዲፈታ የሚጠይቅ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ተጀመረ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 29 ቀን 2010 ዓ/ም) በእስር ላይ የሚገኘው እውቁ የነጻነት ታጋይ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲፈታ የሚጠይቅ የፌስ ቡክ ዘመቻ ዛሬ ተጀምሯል። የአቶ አንድርጋቸው የትግል አጋሮች፣ ስለ ጓዳቸው የሚያስታወሱትን በማጻፍ፣ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ደግሞ እሱ ከጻፋቸው ጽሁፎች ሃሳቦችን በመውሰድ የአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ እየጣሩ ነው።
በራሳቸው ተነሳሽነት የፌስቡክ ዘመቻውን ከመጀመሩት መካከል መምህርትና ጋዜጠኛ መስከረም አበራ አንዷ ናት። መስከረም የሚዲያ ዘመቻው ያስፈለገበት ምክንያት “አንዳርጋቸው ይፈታል ብለው ጠብቀው እስካሁን ባለመፈታቱ እንዲሁም በእሱ ጉዳይ ዝም ሲባል ህዝቡም በአገዛዙ በኩል የሚቀርበውን ውንጀላ ተቀብሎታል የሚል መረዳት እንዳይፈጠር መሆኑን ተናግራለች።
“አንዳርጋቸው ብዙ ፖለቲከኞች የሚሮጡለትን ልታይ ባይነት፣ እኔ ልቅደም፣ እኔ… የሚለው ነገር በፍጹም የለሌበት ሰው ነው። አንዳርጋቸው የሚሮጠው ለሸክም ነው። ሌላው ለስልጣን ሲሮጥ እሱ ከሁዋላ ሆኖ የሚኖረጠው ለመሸከም ነው” የምትለው መስከረም፣ አንዳርጋቸው ያጣነው ሰው ትላለች።
መምህርት መስከረም በአንዳርጋቸው ዙሪያ ሰዎች የሚያስቡትን አያወጡትም ትላለች። ይህ ደግሞ ለአሳሪዎች የልብ ልብ እንደሚሰጣቸው ትናገራለች። ዘመቻው አንዳርጋቸውን ያስፈታዋል ብላ ብታሰብም፣ ያሰሩት ሰዎች አንዳርጋቸው ምን ያክል ሰው ልብ ውስጥ እንዳለ ሰው እንዲያውቅ ማድረግ ይቻላል ትላለች።
በማህበራዊ ሚዲያ የሚካሄደው ዘመቻ ለሚቀጥሉት 3 ተከታታይ ቀናት ይቆያል።