(ኢሳት ዜና–መስከረም 25/2010)ሁለት የብሪታኒያ የጠበቆች ማህበራት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር እንዲፈቱ የብሪታኒያ መንግስት ግፊት እንዲያደርግ ጥሪ አቀረቡ።
ዘጋርዲያን ማክሰኞ ዕለት ለንደን ላይ ባቀረበው ዘገባ እንዳመለከተው ሁለቱ የብሪታኒያ የጠበቆች ማህበራት ጥሪያቸውን ያቀረቡት ለብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በጻፉት ደብዳቤ ነው።
የሎው ሶሳይቲ ፕሬዝዳንት ጆ ኤጋንና የባር ካውንስል ሊቀመንበር አንድሪው ላንግዶን በጋራ ለብሪታኒያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በጻፉት የጋራ ደብዳቤ የብሪታኒያ መንግስት አቶ አንዳርጋቸውን ለማስለቀቅ ይበልጥ ግፊት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የብሪታኒያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሌላ ሀገር የሕግ አሰራር ሒደት ውስጥ አሁን ባለበት ሁኔታ ጣልቃ መግባት ጠቃሚ አይደለም ማለታቸው ተመልክቷል።
የብሪታኒያ መንግስት የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ እንደገና በፍርድ ቤት እንዲታይ ግፊት በማድረግ ላይ መሆኑንም የኢሳት ምንጮች ይገልጻሉ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ምላሽ ይህንን መሰረት ያደርገ ሳይሆን እንዳልቀረም ታምኖበታል።
ሆኖም በኢትዮጵያ የፍትህ ስርአት ላይ ጥያቄ የሚያነሱት ምዕራባውያን የፍርድ ሒደቱን እንደአማራጭ መፍትሄ ማየታቸውም የፖለቲካ ምሁራንን ያነጋገረ ሆኗል።
ሁለቱ የብሪታኒያ የጠበቆች ማህበራት ለብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በጻፉት ደብዳቤ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲፈቱ ብሪታኒያ ጣልቃ እንድትገባ የጠየቁት አቶ አንዳርጋቸው ታግተው ከተያዙበት ቀን ጀምሮ እየደረሰባቸው ያለውን ማሰቃየትና የሰብአዊ መብት ረገጣ በመዘርዘር ጭምር ነው።
አቶ አንዳርጋቸው አይናቸው ተሸፍኖና በካቴና ታስረው በጭለማ ውስጥ ከ50 ቀናት በላይ የቆዩበትንም የስቃይ ግዜ የጠበቆቹ ማህበር ደብዳቤ ያስታውሳል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በኢትዮጵያ መንግስት እጅ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ስቃይ የሚቀበለው በፖለቲካ አመለካከቱ ነው በማለት ለጋርዲያን ሀሳባቸውን የሰጡት የሪፕራይቭ ዳይሬክተር ማያ ፎአ ሲሆኑ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ባለቤትም ለብሪታኒያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያስተላለፉት መልዕክት በዘጋርዲያን ዕትም ላይ ሰፍሯል።
የብሪታኒያ መንግስት አቶ አንዳርጋቸው ወደ ባለቤቱና ልጆቹ እንዲመለስ ካላደረገ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ለብሪታኒያ ዕሴቶች አለመቆማቸውንና የዜጋቸውን መብት ማስከበር አለመቻላቸውን ያረጋግጣል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።