(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 1/2011) በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሱዳን ዴስክ ከፍተኛ ኤክስፐርት የሆኑት አቶ አንዳርጉ ኢያሱ በርሔ ራሳቸውን ከሕወሃት አባልነት ማግለላቸውን አስታወቁ።
የራያ አካባቢ ተወላጅና የሕወሃት አባል የሆኑት አቶ አንዳርጉ ኢያሱ ሕወሃት በራያ ሕዝብ ላይ የማይፈጽመው ኢሰብአዊ ድርጊት ራሳቸውን ከሕወሃት አባልነት ለማግለል ምክንያት እንደሆናቸው ገልጸዋል።
ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ /ሕወሃት/ከለውጡ ጋር ከመተባበር ይልቅ ለውጡን ለመቀልበስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እየተመለከቱ ከዚህ ድርጅት ጋር መቀጠል ስህተት ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ጭምር ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሱዳን ዴስክ ከፍተኛ ኤክስፐርት የሆኑት አቶ አንዳርጉ ኢያሱ በርሔ ከሕወሃት አባልነት ራሳቸውን ከማግለል ባሻገር ለራያ ሕዝብ መብት በሚደረገው ትግል ውስጥ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል።
አቶ አንዳርጉ ኢያሱ በርሔ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኤክስፐርትነት ከመመደባቸው በፊት በኬንያ ናይሮቢ ለአራት አመታት በዲፕሎማትነት ማገልገላቸውንም መረዳት ተችሏል።
በሳምንቱ መጀመሪያ የሕወሃት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ዛዲግ አብርሃ በተመሳሳይ ራሳቸውን ከሕወሃት ማግለላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
በሚኒስትር ድኤታነት የዲሞክራታይዜሽን ማዕከል አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዛዲግ አብርሃ ሕወሃት ከለውጡ በተቃራኒ መቆሙና በራያ ሕዝብ ላይ የሚያደርሰው በደል ራሳቸውን ለማግለል ምክንያት እንደሆናቸውም ተናግረዋል።