የካቲት ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኦሮምያ ክልል ፕሬዚዳንትነቱን ስልጣን ሳያስረክቡ እንዳስረከቡ ተደርጎ የተነጠቁት አቶ አለማየሁ አቶምሳ ታይላንድ ባንኮክ ውስጥ በጥብቅ የህክምና ክትትል ወይም (ኢንቴንሲቭ ኬር ዩኒት) ውስጥ እንደሚገኙ ኢሳት አረጋግጧል።
ግለሰቡ ያለመሳሪያ ድጋፍ በራሳቸው መተንፈስ እንደማይችሉ ፣ ሰዎችን እንደማያናግሩና በዶክተሮች ከፍተኛ ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኙ እኩለቀን ላይ አንድ የሆስቲታሉ ሰራተኛ ለኢሳት ተናግረዋል።
አቶ አለማየሁ ከኦህዴድ የምክር ቤት አባላት ጋር በክልሉ ስለሚታየው ሙስናና የመልካም አስተዳደር መበላሸት ጭቅጭቅ የተሞላበት ስብሰባ ካደረጉ በሁዋላ ወንበራቸው ላይ እንደተቀመጡ ራሳቸውን መሳታቸው ይታወቃል።
በወቅቱ አብረዋቸው የነበሩት አዲሷ የኦህዴድ ምክትል ሃላፊ ወ/ሮ አስቴር ማሞ አቶ አለማየሁ ገርጂ በሚገኝ ሆስፒታል አስቸኳይ ህክምና እንዲያገኙ ከተደረገ በሁዋላ ሆስፒታሉ ወደ ውች እንዲላኩ ማዘዙንና ማምሻውን ወደ ውጭ እንዲላኩ ተደርጓል። ባንኮክ ከደረሱበት እለት ጀምሮ አቶ አለማየሁ ራሳቸውን በመሳት ሰዎችን ለማነጋገር ሳይችሉ ቀርተዋል። ባለቤታቸው ከጎናቸው በመሆን እያስታመሙዋቸው መሆኑንም ኢሳት ለመረዳት ችሎአል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሚቀጥለው ሳምንት የሚደረገው የኦሮሚያ ምክር ቤት ስብሰባ የአዲሱን የክልሉን ፕሬዚዳንት ሹመት ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላ ዜና ደግሞ በመልካም አስተዳደርና በሙስና ዙሪያ የኦሮምያ ክልል ሲቪል ሰርቪስ አባላት ባለፈው ቅዳሜ በአዳማ ከተማ ለስብሰባ ቢጠሩም አብዛኛው ሰራተኛ ሊገኝ ባለመቻሉ በድጋሜ እንዲጠራ ተወስኗል።
በስብሰባው ላይ የተገኙ አንዳንድ የመንግስት ሰራተኞች ” ዘወትር ከማውራት ውጭ ምንም የሚገኝ መፍትሄ የለም፣ የእረፍት ጊዜያችንንም በከንቱ ማባከን” የለብንም በማለት ሲናገሩ ተደምጠዋል።
በስብሰባው ላይ ያልተገኙት ሰራተኞች በሚቀጥለው ስብሰባ ላይ የማይገኙ ከሆነ እርምጃ ይወሰድባቸዋል ተብሎአል።