አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከገቢዎችና ጉምሩክ የቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣናት የሙስና ክስ ጋር በተያያዘ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ከባለሃብቶች ጋር የነበራቸው ቁርኝት የልማታችን ጸር ነበር አሉ፡፡

ጥቅምት (ሰባት)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-አቶ ኃ/ማርያም ዛሬ ጠዋት የአገር አቀፍ የጸረ ሙስና ጥምረት 2ኛ መደበኛ ስብሰባ በሸራተን አዲስ በተካሄደበት ስነስርኣት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር አንዳንዶቹ ባለሃብቶች ከከፍተኛ መንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ሳይቀር የጠበቀ ቁርኝት ፈጥረው እንደነበር አምነው በዚህም ምክንያት ሰዎቹን መንግስት አይደፍራቸውም ተብሎ በህብረተሰቡ ዘንድ እስከመገመት ደርሶ ነበር ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እንደዚህ ዓይነት የመንግስት ባለስልጣናትና ኪራይ ሰብሳቢ ባለሃብቶች ቁርኝታቸውን መርህ አልባ ነው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ ይህ የልማታችን ጸር መሆኑ በስፋት የሚታወቅ ነበር ብለዋል፡፡

ከመሬት አቅርቦት ጋር ተያይዞ ይታዩ የነበሩ ብልሹ አሰራሮች መቀረፋቸውና ሙስናን በተመለከተ የተሠራው ስራ ፍሬ ማፍራት ጀምሮአል ያሉ ሲሆን አስካሁን የተሰሩ ስራዎች ተደምረው ሲታዩ የመንግስታችንን በጸረ ኪራይ ሰብሳቢነትና በጸረ ሙስና ትግሉ ላይ ያለውን ቁርጠኝነትና የማያወላዳ አቁዋም ያመለክታል ሲሉ መንግስታቸውን አንቆለጻጽሰዋል፡፡

ሙስናን ለመታገል ሕዝቡ በጸረ ሙስና ትግሉ ተደራጅቶ እንዲሳተፍ ማድረግ እንደሚገባ አቶ ኃ/ማርያም ጠቁመው በዚህ ረገድ በመንግስት በኩል የመዘግየት ድክመት መኖሩን በማስታወስ በቀጣይ ይህ ስራ በማጠናከር ትግሉ ሕዝባዊ መሰረት እንዲኖረው እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

የአቶ ኃ/ማርያም አስተዳደር በመንግስት አስተዳደር ውስጥ ከላይ እስከታች በከፍተኛ ደረጃ በተንሰራፋው ሙስና ላይ ፈራ ተባ እያለ መውሰድ የጀመረው እርምጃ ከአቶ መለስ አስተዳደር ጋር ሲነጻጸር የተሻለ መሆኑን አንዳንድ ወገኖች
ሲገልጹ የቆዩ ቢሆንም እርምጃው በገቢዎችና ጉምሩክ እንዲሁም በአዲስአበባ ከተማ መሬት አስተዳደር ጥቂት ሹመኞችንና ባለሃብቶችን ብቻ በማሰር የተጠናቀቀ መምሰሉ ከፍተኛ ትችት እያስከተለበትና የመንግስትን ቁርጠኝነት ጥያቄ እያስነሳበት ይገኛል፡፡