አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሶማሊያው ፕሬዚዳንት ጋር የሰጡት መግለጫ የሶማሊ ላንድን ባለሥልጣናት አስቆጣ።

ግንቦት ፫ ( ሦስት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው ሳምንት አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት መሀመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ወደ አዲስ አበባ መጥተው በነበረበት ወቅት በሰጡት የጋራ መግለጫ ላይ አቶ ኃይለማርያም ፦” ከ እንግዲህ ኢትዮጵያ የሶማሊያ ፌዴራል መንግስትን ሳታስፈቅድ ከሌሎች የሶማሊያ ትናንሽ ክልሎች ጋር ግንኙነት አታደርግም” ማለታቸው ነው የሶማሊ ላንድን ባለሥልጣናትና ሕዝብ እያነጋገረ ያለው።
አቶ ኃይለማርያም አክለውም ፦” ዓለማቀፉ ማህበረሰብም ለሶማሊያ ፌዴራል መንግስት ክብር ሊሰጥና ከሌሎች ትናንሽ የሶማሊያ ክልሎች ጋር ግንኙነት መፍጠር ሊያቆም ይገባል” ብለዋል።
ሶማሊ ላንድ በመንግስታቱ ድርጅትና በዓለማቀፉ ማህበረሰብ እንደ ሀገር እውቅና ባይሰጣትም ከሶማሊያ ተለይታ ራሷን ማስተዳደር ከጀመረች 26 ዓመታት ማለፋቸው ይታወቃል። ባለፉት ዓመታት ከሶማሊ ላንድ ጋር እንደ ሀገር ግንኙነት ፈጥረው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት ሀገራት መካከልም አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ የሚታወቅ ሲሆን፤ ጥቂት የማይባሉ የገዥው ፓርቲ ሰዎች ወደ ሶማሊ ላንድ እየተመላለሱ ንግዳቸውን እያጧጧፉ እንደሚገኙ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።
እውነታው ይህ በሆነበት ሁኔታ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ጋር መግለጫ ሢሰጡ “ከእንግዲህ ያለ ሶማሊያ መንግስት እውቅና ከትናንሽ የሶማሊያ ክልሎች ጋር አንገናኝም” ማለታቸው፤ የሶማሊ ላንድን የራስን በራስ የማስተዳደር ነጻነት መቃወማቸው እንደሆነ አድርገው ነው የሶማሊ ላንድ ባለሥልጣናት የቆጠሩት።
ይሁንና ስለ ጉዳዩ የሶማሊ ላንድ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ያሲን ሀጂ መሀመድ ሂሪ ፋራቶን- ከጀስካ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ “የአቶ ኃይለማርያም ንግግር ምንም አያሣስበንም። ምክንያቱም ሶማሊ ላንድ የሶማሊያ አካል አይደለችምና” ብለዋል።
ፋራቶን አክለውም ፦”ኃይለማርያም ሶማሉ ላንድ ብለው ቃል በቃል እስካልጠሩ ድረስ ትኩረት አንሰጠውም” ብለዋል። በተባበሩት የአረብ ኢምሬይት እና በሶማሊ ላንድ መካከል የተፈጠረውን ጠንካራ ግንኙነት በመቃወም በኩል እያደረጉት ላለው ጥረት ከአካባቢ ሀገራት ድጋፍ ለማሰባሰብ በጀመሩት ዘመቻ መሰረት ነው አዲሱ የሶማሊያ መሪ ፕሬዚዳንት ፋርማጆ ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙት።
ምክንያቱም የተባበሩት አረብ ኢምሬይት በክልሉ እያደረገችው ባለው እንቅስቃሴ የሶማሊያ መንግስትና ኢትዮጵያ ደስተኞች ካለመሆናቸውም በላይ ከጀርባ ከፍተኛ ተቃውሞ እያደረጉ ነው።
የፖለቲካ ተንታኞች የተባበሩት አረብ ኢምሬይት በአካባቢው በምታደርገው ጥረት የኢትዮጵያ ተቃውሞ ያዬለው ክልሉን ለመቆጣጠር ያላትን እቅድና ህልም ስለሚያጨናግፍባት ነው ማለታቸውን የናሽናል ዘገባ ያመለክታል።