(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 6/2010) በሞያሌ ከተማ በመከላከያ ሰራዊት የተፈጸመው ግድያ በስህተት የሆነ አይደለም ያሉት የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ታየ ደንዳአ መታሰራቸው ተነገረ፡፡
አቶ ታየ በፌዴራል ፖሊስ አባላት የታሰሩት አዲሱ ገበያ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ወደ ስራ ሲሄዱ መሆኑን ቤተሰቦቻቸው ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ በቅርቡ በሞያሌ ከተማ የተፈጸመውን ግድያ ማውገዛቸው ይታወቃል።
በመከላከያ ሰራዊት አባላት በግፍ የተገደሉት ከ13 በላይ የሞያሌ ከተማ ነዋሪዎች በስሕተት አይደልም ማለታቸውም ይታወሳል።
“የመከላከያም ሆነ የኮማንድ ፖስቱ አዛዦች በህግ ሊጠየቁ ይገባል” ማለታቸውም ለእስር እንደዳረጋቸው የብዙዎች ግምት ነው።
የአቶ ታዬ ባለቤት ወይዘሮ ስንታየሁ አለማየሁ ለቢቢሲ አማርኛው ክፍል እንደተናገሩት ባለቤታቸው መታሰራቸውን እንጂ የት እንደሚገኙ የሚያውቁት ነገር የለም።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ አቶ ታየ ደንዳኣ የታሰሩበት ጉዳዩ በግልጽ አይታወቅም ቢባልም በሞያሌው ጉዳይ ላይ ከኮማንድ ፖስቱ እውቅና ውጭ ለጀርመን ድምጽ ሬድዮ መግለጫ መስጠታቸው ሳይሆን አይቀርም።
አቶ ታየ ግድያው የተፈጸመው በስህተት ሳይሆን ሆን ተብሎ ነው ያሉትም በዚህ መልኩ ነበር።
በኮማንድ ፖስቱ መመሪያ መሰረት ክልሎች በጸጥታ ጉዳይ ላይ መግለጫ መስጠት አይችሉም።
አቶ ታየ ደንዳአ ከቤታቸው ወደ ስራ ለማምራት በጠዋት ሲንቀሳቀሱ በፌዴራል ፖሊስ አባላት ተከበው መያዛቸው ነው የተነገረው።
አቶ ታየ የፌዴራል ፖሊስ በቄሮች ላይ ጥናት ጀምሬያለሁ ባለ ጊዜም በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የምናወቀው ነገር የለም፣ ፌዴራል ፖሊስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አገባው ማለታቸውም ይታወሳል።
ከዚህ ቀደምም የዩንቨርስቲ ተማሪ እያሉ በአሸባሪነት ሰበብ ለበርካታ ጊዜያት ታስረው እንደሚያውቁ የተነገረላቸው አቶ ታየ ይህንኑም በተመለከተ ለቢቢሲ አማርኛው ክፍል መግለጫ ሰጥተው እንደነበር ዘገባው አስታውሷል።
በዩንቨርስቲ ተማሪነታቸው ጊዜ ለሶስት አመታት ታስረው ከቆዩ በኋላ ግን በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ነጻ መባላቸውም ነው የተነገረው።
በዚሁም ምክንያት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ተማሪ የነበሩት አቶ ታየ ደንደአ በተደጋጋሚ ጊዜ እስር ይደረሰባቸው ስለነበር አራት አመታት ይፈጅ የነበረው ትምህርት 16 አመታት እንደጨረሰባቸው ለማወቅ ተችሏል።