(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 19/2010)በብአዴን የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ግንባር ቀደም ተብለው ከሚጠቀሱት አንዱ መሆናቸው የተገለጸው አቶ ተስፋዬ ጌታቸው በሕክምና ላይ እያሉ ሕይወታቸው አለፈ።
የብአዴን ጽሕፈት ቤት ሃላፊና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የሕዝብ ግንኙነትና አደረጃጀት አማካሪ አቶ ተስፋዬ ጌታቸው በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በሕክምና ላይ እያሉ ትላንት ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።
የብአዴን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና ከግንባር ቀደም የለውጥ አራማጆች አንዱ መሆናቸው የሚጠቀሰው አቶ ተስፋዬ ጌታቸው በአማራ ክልል ቴሌቪዥን ከአመት በፊት በሰጡት መግለጫ በአማራ ክልል ኤሌክትሪክ እንዳይስፋፋ ሲደረግ የነበረውን አድሎ ማጋለጣቸውንም ከቪዲዮ ዘገባው ማስታወስ ተችሏል።
“በኢትዮጵያ በአራት አመታት 92 የሃይል ማከፋፈያዎች ሲሰሩ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2015 ብቻ ደግሞ 45 ያህል ማከፋፈያዎች ሲገነቡ በአማራ ክልል በአስር አመት ውስጥ አንድ ማከፋፈያ እንኳን አልተገነባም”በማለት የተናገሩት በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን በስፋት ተሰራጭቶ መወያያ እንደነበርም ማስታወስ ተችሏል።
ለህክምና ወደ አሜሪካ ከመጡ ወራት ያስቆጠሩትና በዚህ በዋሽንግተን ዲሲ ሕክምና ላይ ኣያሉ ሕይወታቸው ያለፈው የአቶ ተስፋዬ ጌታቸው አስከሬን ነገ አርብ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚሸኝም መረዳት ተችሏል።