አቶ በከር ሻሌ የኦህዴድ ጽ/ቤት ሃላፊ ሆነው ተሾሙ

የካቲት ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በእስር ላይ የሚገኙትን አቶ መላኩ ፋንታን በመተካት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ከሶስት አመታት በፊት የተሾሙት አቶ በከር ሻሌ ፣ ከዛሬ ጀምሬ የኦህዴድ ድርጅት ጽ/ቤት ሃላፊ ሆነው መሾማቸውን ፎርቹን ዘግቧል።በኦሮምያ በመካሄድ ላይ ያለውን ተቃውሞ ተከትሎ ፣ አቶ በከር የክልሉን ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድርን ይተካሉ ተብሎ በስፋት ሲወራ ቆይቷል። ይሁን እንጅ ፎርቹን እንዳለው ግለሰቡ ጽ/ቤቱን ለአንድ አመት ብቻ የመሩትን አቶ ዳባ ደበሌን ተክተው እንዲሰሩ ተሹመዋል።አቶ ዳባ ደበሌ ለምን እንደተነሱና በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ጋዜጣው የዘገበው ነገር የለም። አቶ በከር የምእራብ አርሲ ፣ ዶዶላ ከተማ ተወላጅ ሲሆኑ፣ ስራቸውን የጀመሩት የወረዳው አስተዳዳሪ በመሆን ነው።በመቀጠልም፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር፣ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ዲኤታ እና የአዳማ ከንቲባ ሆነው ሰርተዋል።
በኦሮምያ በተለይም በምስራቅና ምእራብ ወለጋ፣ በአርሲ፣ በአምቦ፣ ወለጋና ቦረና አካባቢዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአጋዚ ወታደሮችና የፌደራል ፖሊሶች ሰፍረው ይገኛሉ።በዚህ ሳምንት መግቢያም በወለጋ አንዳንድ አካባቢዎች ተማሪዎች ተቃውሞ ሰልፎችን አድርገዋል። ባለፉት ሁለት ዋረት በነበረው ተቃውሞ ከ250 ያላነሱ ሰዎች መገደላቸው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ መታሰራቸው ይታወቃል።
በተለይም በአዳማ እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ እስረኞች ከቤተሰቦቻቸው ምንም አይነት ምግብ እንዳይገባላቸው ታግዶ የቆየ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ተቀያሪ ልብስም እንዳይገባላቸው መከልከሉን ዘጋቢያችን ገልጿል።