አቶ በቀለ ገርባ በጽኑ ታመሙ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 16/2010)

በእስር ላይ የሚገኙት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ በጽኑ መታመማቸው ተነገረ።

የእስር ቤት ባለስልጣናትም አቶ በቀለ ገርባ ሕክምና ወደሚያገኙበት ሆስፒታል እንዳይሄዱ ማገዳቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

አቶ በቀለ ገርባ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ቢኖራቸውም መራመድ ባለመቻላቸው የፍርድ ሂደቱ ተስተጓጉሏል ተብሏል።

ታዋቂው ፖለቲከኛ አቶ በቀለ ገርባ ክሳቸው ከሽብር ወንጀል ሕገመንግስትን በሃይል ለማፍረስ በመምከር ወደሚል ቢቀየርላቸውም እስካሁን የዋስ መብታቸው አልተጠበቀላቸውም።

ቀደም ሲል በከፍተኛው ፍርድ ቤት የዋስ መብታቸው እንዲከበር ተወስኖ ነበር።

ሆኖም ግን አቃቢ ሕግ ይግባኝ በመጠየቁ በእስር ላይ እንዲቆዩ ተገደዋል።

አሁን ደግሞ አቶ በቀለ ገርባ በጽኑ መታመማቸው ነው የተነገረው።

ልጃቸው ቦንቱ በቀለ ለጀርመን ድምጽ ሬዲዮ እንዳለቸው አቶ በቀለ ገርባ በፊት የነበረባቸው የደም ግፊት አሁን ላይ ጸንቶባቸዋል።

ከትላንት በስቲያ ስትጎበኛቸውም የራስ ምታትና የአንገት ህመም አለብኝ እንዳሏት ነው የገለጸችው።

ቆሞ ለማውራትም አይችልም ብላለች።

አቶ በቀለ ገርባ ሕክምና ለማግኘት ወደ ሆስፒታል ለመሄድ ቢጠይቁም ፈቃድ እንዳላገኙና እንድተከለከሉ ወይዘሪት ቦንቱ ተናግራለች።

ይባስ ብሎ የእስር ቤቱ ባለስልጣናት ስብሰባ አድርገው በቀን አንድ ጊዜ የሚወስደውን መድሃኒት ሁለት ጊዜ ይውሰድ ብለው መወሰናቸውን ልጃቸው በመገረም ገልጻለች።

እንሱ ይህን ይበሉ እንጂ እሱ ግን በቀን ሁለት ጊዜ መድሃኒቱን ሲወስድ ችግር ስለሚያመጣበት ይህን ማድረግ አይችልም ነው ያለችው።

ሕክምና የተከለከሉበት ምክንያት እንዳልተነገራቸውም ልጃቸው ቦንቱ ተናግራለች።

እናም ጉዳዩን ለፍርድ ቤት እናመለክታለን፣በጠበቃችን በኩልም ጉዳዩን እየተከታተልን ነው ብላለች።

በድጋሚ ከታሰሩ ሁለት አመታትን ያስቆጠሩት አቶ በቀለ ገርባ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ የተባለበትና ውድቅ የተደረገው የዋስትና መብታቸው ነገ ታህሳስ 17/2010 እንደሚታይ ለማወቅ ተችሏል።