(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 20/2010)የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ በዋስ እንዲፈቱ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወሰነ።
ነገ ከወህኒ ይወጣሉም ተብሎ ይጠበቃል።
የወህኒ ቤቱ ሃላፊዎች አንዳንዴ ከህግ በላይ ስለሚሆኑ የሚሆነውን እናያለን፣አባቴ በዋስትና በመፈታቱ ግን እፎይታ ተሰምቶኛል ስትል ልጃቸው ቦንቱ በቀለ ለአዲስ ስታንዳርድ አስተያየቷን ሰጥታለች።
በኦሮሚያ ክልል ከተካሄደው አመጽ ጋር በተያያዘ በታህሳስ 2008 ወደ ወህኒ የወረዱት አቶ በቀለ ገርባ ከታሰሩ ከአንድ አመት ከ10 ወራት በኋላ በዋስትና እንዲፈቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የወሰነው ዛሬ ጥቅምት 20/2010 ሲሆን የ30ሺ ብር ዋስትና እንዲያቀርቡም ተጠይቋል።
በአባቷ መፈታት እፎይታ እንደተሰማት ለአዲስ ስታንዳርድ የገለጸችው የአቶ በቀለ ገርባ ልጅ ቦንቱ በቀለ ነገ አባቷን በነጻነት እንደምታገኝ ያላትን ተስፋ ገልጻለች።
ሆኖም በዋስ ይፈታ እንጂ የቀረቡበት ክሶች ከባድና ፍርድ ቤቶቹም በፖለቲካ የተቃኙ በመሆናቸው ቀጣዩ ሁኔታ ያሳስበኛል ስትል አክላለች።
የማረሚያ ቤቱ ሃላፊዎች አንዳንዴ ከሕግ በላይ ስለሚሆኑ የሚከተለውን ባላውቅም በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሰረት ይወጣል የሚል እምነት አለኝ በማለትም አስተያየትዋን ሰጥታለች።
የዛሬ ሁለት አመት በኦሮሚያ ክልል ከተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ አመጹን በማቀነባበርና በመምራት እንዲሁም በኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባልነት በመወንጀል ወደ ወህኒ የተጋዙት የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ በሚያዚያ ወር 2008 ከሌሎች 21 ተከሳሾች ጋር የአሸባሪነት ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ፍርድ ቤቱ በሂደት በአቶ በቀለ ገርባ ላይ የቀረበውን የሽብር ክስ ወደ ወንጀል ክስ ዝቅ በማድረጉ በጠበቆቻቸው አማካኝነት የዋስትና ጥያቄ አቅርበዋል።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረጉ አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረቡት አቶ በቀለ ገርባ ዛሬ በ30ሺ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱ አዟል።
አቶ በቀለ ገርባ በ2003 በተመሳሳይ ተከሰው ለ4 አመታት ወህኒ ቤት መቆየታቸው ይታወሳል።