አቶ በቀለ ገርባ በዋስትና እንዲወጡ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሰጠው ትዕዛዝ ታገደ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 22/2010)የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ በቀለ ገርባ በዋስትና እንዲወጡ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሰጠው ትዕዛዝ ታገደ።

በእስር ቤት እንዲቆዩም ተወስኗል።

ርምጃው የተወሰደው ቤተሰቦቻቸው የተጠየቀውን ዋስትና አሟልተው ይፈታሉ ብለው በሚጠብቁበት ወቅት እንደሆነም ታውቋል።

የአቶ በቀለ ዋስትና መታገዱን ይፋ ያደረገው የሕወሃቱ ኢፈርት ንብረት የሆነው ሬዲዮ ፋና ነው።

ሰኞ ጥቅምት 20/2010 በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ30 ሺ ብር ዋስትና ጠርተው እንዲወጡ የተወሰነላቸው አቶ በቀለ ገርባ ከሁለት ቀናት በኋላ ዋስትናቸው በሰበር ሰሚ ችሎት እንደታገደ መገለጹ ከሀገሪቱ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንጻር ሕገ ወጥ ሲሉ የሕግ ባለሙያዎች በመተቸት ላይ ናቸው።

ዋስትናው የተፈቀደው በፖለቲካ ውሳኔ ነው የሚሉት ወገኖች ደግሞ ዋስትናውም የታገደው በተመሳሳይ በፖለቲካ ውሳኔ ነው የሚል አስተያየትን ሰጥተዋል።

አቶ በቀለን መፍታት የፖለቲካ ውጥረቱን ያረግባል የሚለው አካል በዋስትና እንዲወጡ ሲፈልግ ፍርድ ቤቱን መጠቀሚያ እንዳደረገው ሁሉ፣ ዋስትናው እንዲነሳ የተንቀሳቀሰው ሌላው ቡድንም በተመሳሳይ ፍርድ ቤቱን መጠቀሙን ያስረዳሉ።

አቶ በቀለ ገርባ የዋስትና ጥያቄውን ማሟላታቸውን ተከትሎ እርሳቸውን ከእስር ላለመልቀቅ በቅድሚያ ወህኒ ቤቱ የታሰሩበትንና ዋስትና ያገኙበትን ፋይል ቁጥር የተለያየ ነው በሚል ጉዳዩን ለተጨማሪ አንድ ቀን ካራዘመ በኋላ የሰበር ሰሚ ችሎቱ እግድ መከተሉም ተመልክቷል።

የሀገሪቱን የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነ ስርአትን በመጥቀስ አስተያየታቸውን የሰጡ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ በይግባኝ የተሰጠ ዋስትና በድጋሚ ይግባኝ አይጠየቅበትም።-ለዚህም ደግሞ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአት ቁጥር 75ትን ይጠቅሳሉ።

አቶ በቀለ ገርባ በዋስትና እንዲፈቱ መወሰኑን ተከትሎ ልጃቸው እለቱን ለአዲስ ስታንዳርድ አስተያየቷን ስትሰጥ ማረሚያ ቤቱ አንዳንዴ ከህግ በላይ ይሆናና ከዚህ ጋር በተያያዘ ላይፈቱም እንደሚችሉ ያላትን ጥርጣሬ መግለጿን መዘገባችን ይታወሳል።

አቶ በቀለ ገርባ ለሁለተኛ ጊዜ ወህኒ ከወረዱ የፊታችን ታህሳስ 2 አመት የሚሞላቸው ይሆናል።

ቀደም ሲልም ለአራት አመታት በተመሳሳይ መታሰራቸው አይዘነጋም።