አቶ በቀለ ገርባና ሌሎች ተከሳሾች ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ተነገረ

ኢሳት (ህዳር 2 ፥ 2009)

በወህኒ ቤት የሚገኙ የኦፌኮ ም/ፕሬዚደንት አቶ በቀለ ገርባና ሌሎች ተከሳሾች በእስር ቤት ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ተገለጸ። አርብ ህዳር 2 ቀን 2009 ፍ/ቤት መቅረብ ከሚገባቸው 22ቱ ተከሳሾች ውስጥ አምስቱ በችሎት ያልተገኙ ሲሆን፣ ከመካከላቸው አንደኛው የት እንደሚገኙ አላውቅም ሲል አቃቤ ህግ ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል።

በችሎቱ ሳይገኙ ከቀሩት አምስቱ ተከሳሾች ማለትም ገላና ነገራ፣ ገመቹ ሻንቆ እንዲሁም ደረጀ መርጋ እና ፍሮምሳ አብዲሳ በሸዋ ሮቢት ወይንም በዝዋይ እንደሚገኙ ለችሎቱ ያስታወቀው ከሳሽ አቃቤ ህግ የትኛው ተከሳሽ በትክክል በየትኛው እስር ቤት እንደሚገኝ አለማስታወቁን ከአዲስ ስታንዳርድ የእንግሊዝኛ መጽሄት ዘገባ መረዳት ተችሏል።

ሌላው በችሎቱ መገኘት ሲገባቸው ያልተገኙት አቶ ጪምሳ አብዲሳ ሲሆኑ፣ ፖሊስም ሆነ አቃቤ ህግ ተከሳሹ የት እንዳሉ አናውቅም ማለታቸው ተመልክቷል። ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋለውን ግለሰብ የት እንዳለ አላውቅም ሲል መግለጫ መስጠቱ ያልተለመደ በመሆኑ፣ የተከሳሽ ደህንነት አሳሳቢ ሆኗል።

በነሃሴ ወር መጨረሻ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ከተነሳ የእሳት ቃጠሎ ጋር በተያያዘ መንግስት እንዳመነው 23 ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ ከመካከላቸው ሁለቱ ሊያመልጡ ሲሉ በጥይት ተገድለዋል።

ገለልተኛው የሰብዓዊ መብት ፕሮጄክት ከቂሊንጦው ቃጠሎ ጋር በተያያዘ 67 ሰዎች መገደላቸውን የገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 45ቱ በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን ማስታወቁን አዲስ ስታንዳርድ በዘገባው አስታውቋል።

ድብደባ እንደተፈመባቸው ለችሎት ያስታወቁት አቶ በቀለ ገርባ ለፊታችን ማክሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ የተሰጣቸው ሲሆን፣ ቀጠሮ የተያዘው የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት እንደነበርም ተመልክቷል። ሆኖም አቃቤ ህግ ምስክሮቹን ይዞ ባለመቅረቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሌሎች የኦፌኮ አመራሮችና አባላት ከታሰሩ የፊታችን ታህሳስ አንድ አመት ይሞላቸዋል። አቶ በቀለ ገርባ ቀደም ሲል የተፈረደባቸውን እስራት ጨርሰው የወጡት በመጋቢት ወር 2007 ሲሆን፣ በ8 ወር ጊዜ ውስጥ እንደገና ተመልሰው ታስረዋል።

አቶ በቀለ ገርባ ወደ ወህኒ የወረዱት ከአዲስ አበባ ኦሮሚያ ክልል የተቀናጀ ማስተር ፕላን በመቃወም ከተነሳው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ሲሆን፣ መንግስት ማስተር ፕላኑን ሰርዣለሁ ቢልም፣ በእነሱ ላይ የቀረበው ክስ ቀጥሏል። ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጋር ግንኙነት አላችሁ የሚል የሽብር ክስ እንደቀረበባቸውም ይታወሳል።