አቶ በረከት ስምኦን መንግስታቸው ስካይፒንና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ለመዘጋት መወሰኑን አመኑ

ሰኔ ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ሽመልስ ከማል መንግስት ስካይፕንና የኢንተርኔት አገልግሎትን ለመዝጋት ወስኗል በማለት የሚገልጡት የምእራባዊያን ጋዜጠኞች ናቸው በማለት መግለጫ በሰጡ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አቶ በረከት ስምኦን ኢንተርኔት ለቴሌኮም አገልግሎት የመጠቀም ተግባር አገሪቱን ከፍተኛ ገቢ እያሳጣት በመምጣቱ ስካይፒን ጨምሮ ሌሎች የኢንተርኔት የቴሌኮም አገልግሎቶችን መንግስት ለመዝጋት ወስኗል ብለዋል።

የመንግሥት የኮምኒኬሸን ሚኒስትር የሆኑት አቶ በረከት ለኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች በተዘጋጀ ሥልጠና ላይ ሰሞኑን እንደተናገሩት መንግስት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የስካይፒ ዓይነት አገልግሎቶች በቴሌኮሚኒኬሸን ዓመታዊ ገቢ ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳደራቸው ነው፡፡

አቶ በረከት በእርምጃው የተቃጣውን ትልቅ ገቢ በመመለስ ለተያዙት የባቡር ፣ የስኳርና ሌሎች ፕሮጀክቶች ለመደጎም መታቀዱን ለጋዜጠኞቹ ነግረዋቸዋል፡፡

በኢንፎርሜሸን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ተረቅቆ ለፓርላማ በቅርቡ የቀረበው የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀልን የሚመለከተው ረቂቅ አዋጅ በህገወጥ የቴሌኮም አገልግሎት አገሪቱ እስከ 83 በመቶ የሚሆን ገቢ እንደምታጣ በመጥቀስ በዚህ ወንጀል ውስጥ ተሰማርቶ መገኘት ከ10-20 ዓመታት እስራትና በዚህ ሕገወጥ አገልግሎት የተገኘ ገቢ እስከ አስር ዕጥፍ የሚደርስ መቀጮ የሚያስቀጣ መሆኑን ተጠቃሚዎችን ደግሞ ከ3 ወራት እስከ 2 ዓመታት እስራትና እስከ 20ሺ ብር መቀጫ የሚጥል ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት ዓርብ ዕለት በጽ/ቤታቸው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት የአቶ በረከት ምክትል የሆኑት አቶ ሸመልስ ከማል ስካይፒ አለመከልከሉን ፣በየድረገጹ የሚነገረው ሁሉ በሬ ወለደ ነው ሲሉ ማሰተባበላቸው ይታወሳል፡፡ አቶ ሽመልስ ከዚህ ቀደም የአሜሪካንን ደምጽ ለማፈን የመንግስት ዲሞክራሲያዊ ባህሪ አይፈቅድለትም ባሉ በቀናት ውስጥ አቶ መለስ ዜናዊ ቪኦኤን ማፈናቸውን ተናግረው ነበር። አሁን ደግሞ የአቶ ሽመልስ አለቃ አቶ በረከት ስካይፕንና በኢንትርኔት ስልክ የመደወልን አካሄድ እናስቆማለን ማለታቸው የተለያዩ አስተያየቶች እንዲቀርቡ አድርጓል። አንዳንድ ወገኖች ወይ የመንግስት ባለስልጣናት እርስ በርስ አይነጋገሩም ወይም  አቶ ሽመልስ ዬይስሙላ ቃል አቀባይ ናቸው ወይም እርሳቸውን ለማዋረድ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው በማለት አስተያየት ይሰጣሉ።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide