(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 15/2010) የትግራይ ተወላጆች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጋር በመሆን ባቋቋሙት ዳሎል ባንክ ውስጥ ባለድርሻ ተደርገው ስማቸው የተጠቀሰው የአማራው ባለሃብት አቶ በላይነህ ክንዴ በባንኩ ውስጥ ምንም ድርሻ እንደሌላቸው ገለጹ።
ይህም የትግራይ ተወላጆች በባንኩ ወስጥ ያላቸውን የ 63 በመቶ ድርሻ ይበልጥ ከፍ የሚያደርገው ሆኖ ተገኝቷል፥ባንኩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሃብት ለመንቀሳቀስ በመወሰን መቁቋሙንም ኢሳት ምንጮችን በመጥቀስ ባለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ ዘገባ ማቅረቡም ይታወሳል።
በኢትዮጵያ 17ኛው የግል ባንክ ለመሆን በመንቀሳቀስ ላይ ያለው ዳሎል ባንክ ከመነሻው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተርስቲያን አማካኝነት ሊቋቋም የነበረ ነው፣ብሄራዊ ባንክ የዕምነት ተቋማት ባንክ እንዲያቋቋሙ አይፈቀድም የሚል ምላሽ ሲሰጥ፣ ቤተክህነት ከትግራይ ባለሃብቶች ጋር ባንኩን ወደ ማቋቋም አምርታለች፣በዚህ ባንክ ወስጥ የትግራይ ባለሃብቶች 63 በመቶ ድርሻ ሲይዙ ፣ቤተክህነት 19 በመቶውን ወስዳለች።
በዳሎል ባንክ ወስጥ ከፍተኛ ባለድርሻ ተደርገው የተጠቀሱት ብቸኛው የአማራ ባለሃብት አቶ በላይንህ ክንዴ በባንኩ ወስጥ ምንም ደርሻ እንደሌላቸወ በይፋ አስታውቀዋል።
አቶ በላይነህ ክንዴ በሳምንቱ መጨረሻ አዲስ አበባ ከተማ ከሚታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ በዳሎል ባንክ ወስጥ ስላላቸው ድርሻ ተጠይቀው አንድ ብር እንኳን እንደሌላቸው በሚከተለው መልክ ገልጸዋል።
“ አክሲዮን እንድገዛ ተጠይቄ ፈቃደኛ አለመሆኔን ገልጫለሁ፡፡ እኔም በባንኩ ውስጥ እንዳለሁበት ተደርጎ ሲነገር ሰምቻለሁ፡፡ በአጠቃላይ ግን እኔ በአዲሱ ባንክ ውስጥ የአንድ ብር አክሲዮን የለኝም፡፡” ብለዋል።
ይህም ባንኩን ሙሉ በሙሉ የትግራይ ባለሃብቶች እና የቤተክህነት ያደርገዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተክርስቲያናት በተለያዩ ባንኮች ያስቀመጡትን 12 ቢሊዮን ያህል ብር ወደ ዳሎል ባንክ በማዞር ፣በዚህ ለንቀስቀሰ መወሰኑን የቤተክህነት ምንጮች ገልጸዋል ።
በዳሎል ባንክ መመስረቻ ሰነድ ላይ እንደተመለከተው ስማቸው የተዘረዘረው 16 የትግራይ ባለሃብቶችና ኩባንያዎች ብሔራዊ ባንክ ከሚጠይቀው ግማሽ ቢሊየን ብር የ328 ሚሊየን 801 ሺ ብር ድርሻ ይዘዋል።
አቶ አዘዞም አየለ፣አቶ ሃይለስላሴ አምባዬ፣አቶ ብርሃኔ ግደይ፣አቶ አትክልቲ ይህደጎ፣አቶ ታደሰ ደስታ፣አቶ ሙለይ አዲስ፣አቶ ሃጎስ ሃድጉ ገብረእግዚአብሔር እንዲሁም ሙሉ ታምራት እያንዳንዳቸው በ25 ሺ አክሲዮን በግል የ25 ሚሊየን ብር ባለድርሻ መሆናቸውን ለብሔራዊ ባንክ ከቀረበው ሰነድ ላይ መመልከት ተችሏል።
ተካሃፍ ትሬዲንግ፣ታምሪን ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ፣ቢ ኤን ቲ ኢንደስትሪ ኤንድ ትሬዲንግ፣ወርቃ ትሬዲንግ ሃውስ የተባሉ የትግራይ ባለሃብቶች ኩባንያዎችም እያንዳንዳቸው በ25 ሺ አክሲዮን እያንዳንዱ ኩባንያ የ25 ሚሊየን ብር ባለድርሻ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።
አቶ አዲስ ገብረማርያም፣ሙሉ ሚዛን ትሬዲንግ፣አቶ በርሔ ሃጎስ፣ሉችያ ተስፋዬ ገብረመስቀል ደግሞ ከ5 ሚሊየን ብር እስከ 12 ሚሊየን 500 ሺ ብር አክሲዮን መግዛታቸውን መረዳት ተችሏል።
ከዳሎል ባንክ ውስጥ 328 ሚሊየን 801ሺ ብር የ16 የትግራይ ተወላጆችና ኩባንያዎች ድርሻ ሲሆን ፣19 በመቶው የቤተክህነት ድርሻ ከነሱ ጋር በትብብርና በቁርኝት የሚሰሩት እነ መምህር ጎይቶም የተወከሉበት እንደሆነም ተመልክቷል።