አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ሰሞኑን የሰጡትን መግለጫ መኢአድ፦”አሳፋሪ” አለው

ሚያዚያ ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከቤንች ማጅ ዞን ጉራ ፈርዳ ወረዳ ስለተፈናቀሉት የአማራ ተወላጆች አስመልክቶ የደቡብ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ሰሞኑን የሰጡትን መግለጫ መኢአድ፦”አሳፋሪ” አለው።

አቶ ሽራው ሽጉጤ ጉዳዩን አስመልክተው ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፦”ምንም የተባረረ ሰው የለም። ደን ሲያቃጥሉና ሲጨፈጭፉ የነበሩ 33 ህገ-ወጦች ከክልሉ እንዲወጡ ተደርገዋል” ማለታቸው ይታወሳል።

መኢአድ   እንዳለው ግን ከክልሉ እየተባረሩ ያሉት ሰዎች ደን ያቃጠሉና የጨፈጨፉ ሳይሆኑ፤ በልማት የተሸለሙ፣ ግብር የሚከፍሉና  ሀብት ንብረት ያፈሩ  ናቸው፡፡

ከከልሉ አሁንም ሰዎች እየተሰደዱና እየተፈናቀሉ ፤ከመኖሪያቸውና ከእርሻቸውም እንዲነሱ እየተገደዱ መሆናቸውንም  መኢአድ ጠቁሟል።

ዜጎች በገዛ አገራቸው እየተደበደቡ፣እየተገረፉ፣ በሀሰት እየተከሰሱና እየታሰሩ ነው ያለው መኢአድ፤ በቅርቡ በወረዳው አንድ ሰላማዊ ዜጋ “ኢየሩሳሌም”  ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በፖሊስ በደረሰበት ከባድ ድብደባ ራሱን ስቶና ከመኪና ላይ ወድቆ ህይወቱ ማለፉን በማስረጃ አቅርቧል።

አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፦” ከጉራ ፈርዳ ወረዳ የተፈናቀለ የለም፤ሰዎችንም ለመመለስ የተያዘ እቅድ የለም” በማለት የሰጡት መግለጫ ከእውነት የራቀ መሆኑን የገለጸው መኢአድ፤ “ፀሐይ የሞቀውን እውነት ለመሸፈን የሚደረገው መሯሯጥ፣ በዜጎች ላይ የተፈጸመውን ኢ-ሰብአዊና ኢ-ዴሞክራሲያዊ   ድርጊት  ያድበሰበሰ እንዲሁም የዜጎችን ክብር የነካና ያዋረደ ነው፤” ብሏል፡፡

“የክልሉ ባለሥልጣናት ድርጊት፤  መንግሥት በሕዝብ ላይ ለደረሰው ሰቆቃ ጆሮና ዓይን ሰጥቶ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ፣ በተራ ፕሮፖጋንዳ ላይ በመጠመድ እውነትን ደብቆ በበደል ላይ በደል በመፈጸም፣ እኩይ ተግባር ላይ መሰማራቱን ይጠቁማል›› ያለው መኢአድ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት በሚያስተዳድሩት ክልል ውስጥ በዜጎች ላይ ለተፈጸመው ጥቃት የበላይ መመርያ ሰጭ በመሆናቸው፣ ከማንም በላይ ጉዳዩ በቀጥታ እንደሚመለከታቸው  አስገንዝቧል፡፡

ከአማራ ክልል በተለያዩ ጊዜያት በሥራ ምክንያት ወደ ደቡብ ክልል ቤንቺ ማጂ ዞን እየሄዱ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ፣ በሕጋዊ መንገድ ከመንግሥት መሬት የተረከቡና ሀብት ንብረት ያፈሩ፣ ቤተሰብ የመሠረቱና ግብር ከፋይ  የሆኑ  በሽህ የሚቆጠሩ ዜጎች በተናቀሉበት ሁኔታ  ፣ የደቡብ ክልል  ባለሥልጣናት ቁጥራቸውን ወደ 33 በማውረድ ‹‹ደን ሲያወድሙና ሲያቃጥሉ የነበሩ ሕገወጦች ነቸው›› ማለታቸው አሳዛኝ መሆኑንም መኢአድ ገልጿል፡፡
ዜጎቹ፤  ሕጋዊ ሆነው ይኖሩ እንደነበር የሚያረጋግጥ ሰነድና ግብር የከፈሉበት ማስረጃ በእጃቸው እንደሚገኝ፣ከመካከላቸውም  በ1996 ዓ.ም ወረዳቸው ጉራፈርዳን በልማት ከዞኑ በአንደኝነት ያሸለሙ አምራች ዜጎች  እንደሚገኙበት፣ መንገድ፣ ትምህርት ቤትና ቀበሌዎችን የገነቡ፣ ቤተ ክርስቲያን ያነፁና ከህብረተሰቡ ጋር  መልካም መስተጋብር የፈጠሩ መሆናቸውን መኢአድ አብራርቷል፡፡

ከጉራ ፈርዳ ወረዳ የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች  አዲስ አበባ ገብተው በመኢአድ ፅህፈት ቤት እንደተጠለሉና በቅርቡ ደግሞ ወደ ደብረብርሀንና ሌሎች ከተሞች እንዲጓጓዙ መደረጋቸው ይታወሳል።

________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide