(ኢሳት ዲሲ–ጥር 3/2011)በኢትዮጵያ በተካሄዱ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በገንዘባቸውና በሃሳባቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ የሚታወቁት አቶ ሰለሞን በቀለ አረፉ።
የቀብራቸው ስነስርአትም ነገ በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት ፌርፋክስ ይፈጸማል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት በሃገር ቤት የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶችን በማገዝ፣ተባብረው እንዲሰሩም ድጋፍ በማድረግ ስማቸው የሚጠቀሰው አቶ ሰለሞን በቀለ፣ቅንጅት በተፈጠረበት ወቅትም ከፍተኛ ድጋፍ ካደረጉ ባለሃብቶች ውስጥም ይጠቀሳሉ።
ከ52 አመታት በፊት ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የተጓዙት አቶ ሰለሞን በቀለ በአትላንታ ዩኒቨርስቲና በጆን ማርሻል ሕግ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን መከታተላቸውን ከሕይወት ታሪካቸው መረዳት ተችሏል።
የታክሲና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ባለቤት በመሆን ከጥቁር ባለሃብቶች የመጀመሪያው መሆናቸውም ታውቋል።
አቶ ሰለሞን በቀለ የተለያዩ የንግድ ማዕከላት ባለቤትነትን ጨምሮ በከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ሲሳተፉም ቆይተዋል።
በአሜሪካ ምድር ከሚገኙ ጥቂት ሚሊየነር ኢትዮጵያውያን አንዱ የነበሩትና በገንዘባቸውም በኢትዮጵያ ለውጥ ለማምጣት በሚደረገው ትግል አስተዋጽኦ በማድረጋቸው፣ሕገ መንግስት የመናድ ሙከራ አድርገሃል የሚል ክስ ከቅንጅት መሪዎች ጋር ተመስርቶባቸዋል።
ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት ኢትዮጵያን የለቀቁትና በባዕድ ሃገር 52 አመታት ያሳለፉት አቶ ሰለሞን በቀለ ማክሰኞ ታህሳስ 30/2011 ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።
ነገ ቅዳሜ ጥር 4/2011 ከጠዋቱ 9 ሰኣአት በዋሽንግተን ዲሲ ደብረገነት መድሃኒአለም ቤተክርስቲያን የጸሎተ ፍትሃት ስነስርአት እንደሚካሄድላቸውም ታውቋል።
ከቀኑ 1 ሰኣአት ላይም በቨርጂኒያ ግዛት ፌርፋክስ ከተማ የቀብራቸው ስነስርአት ይፈጸማል።