ታህሳስ 23 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት:- በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ በአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠሪ የነበሩትና በኮ/ል መንግስቱ ሀይለማርያም ይመራ የነበረውን የኢትዮጵያን መንግስት ከ ኢህአዴግና ከሻእብያ ጋር ሲያደራድሩ የነበሩት አምባሳደር ሄርማን ኮህን፣ “መለስ ዜናዊ በምርጫ 97 የተሸነፈ ቢሆንም ፣ የህዝቡን ድምጽ ሰርቆ የመንግስት ስልጣን ይዞአል” ብለዋል። “በዚህም የተነሳ” ይላሉ አምባሳደሩ ፣ “ስልጣን ከመያዙ በፊት የገባውን ቃል አጥፏል።”
አምባሳደር ኮህን ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፣ የመለስ መንግስት ለአማራው ህዝብ ጥላቻ እንዳለውም አልሸሸጉም።
በአንድ ወቅት መሬት በግል ይዞታ ስር እንዲሆን ለመለስ ዜናዊ ሀሳብ ማቅረባቸውን የገለጡት ባለስልጣኑ፣ አቶ መለስ ግን “ኢህአዴግ መሬትን ወደ ግል ይዞታ ለመቀየር የማይፈልገው ከአማራ ለመከላከል ሲል ነው” ብለው እንደመለሱላቸው ተናግረዋል።
“አሜሪካ በ1990ዎቹ መግቢያ የደርግን ውድቀትና የኢህአዴግን አሸናፊነት የተቀበለችው ምንም አማራጭ ስላልነበራት ነው” የሚሉት አምባሳደሩ፣ “በጊዜው የአሜሪካ ዋና ፍላጎት አዲስ አበባ እንዳትጠፋ መከላከል ነበር” ሲሉ አክለዋል።