አቶ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ በቅርቡ የነዳጅ ሀብት ባለቤት እንደምትሆን መናገራቸው ጠንከር ያለ ትችት አስከተለ

ሰኔ ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-አቶ መለስ ዜናዊ በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው የ አለም ኢኮኖሚ ፎረም ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ በቅርቡ የነዳጅ ሀብት ባለቤት እንደምትሆን መናገራቸው ጠንከር ያለ ትችት አስከተለ።

የማዕድን ሚኒስትሯ በበኩላቸው የነዳጅ ዘይት ግኝት ሊረጋገጥ ሚችለው ነዳጁ ተቆፍሮ ሲወጣ ብቻ ነው በማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩን  የችኮላ ንግግር ውድቅ አድርገውታል።

“ከነዳጅ ዘይት ግኝቱ በፊት ወሬው ምነው ቀደመ?” በሚል ርዕስ  ክንፈ ኪሩቤል ተስፋሚካኤል የተባሉ ፀሀፊ በሪፖርተር ላይ ባቀረቡት ጽሁፍ ፤በአገራችን ላለፉት 50 ዓመታት የአሜሪካ፣የጀርመን፣ የሩሲያ፣ የማሌዥያና የሌሎች አገሮች  ኩባንያዎች የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ሲያካሄዱ መቆየታቸውን በማውሳት፤ ከነዚህ መካከል አንድኛቸውም እንኳ ውጤታማ ሲሆኑ አለመታየታቸውን አመልክተዋል።

በቅርቡ እንኳን ፔትሮናስ የተባለ የማሌዥያ  ኩባንያ የደቡብ ሱዳን አጎራባች በሆነው በጋምቤላ ክልል የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ማካሄዱን የጠቀሱት አቶ ክንፈ፤ በወቅቱ ሂደቱ እንደ ደቡብ ሱዳን ሁሉ በጋምቤላ ክልል የዘይት ክምችት ይኖራል ተብሎ ከፍተኛ እምነትና ተስፋ አሳድሮ እንደነበር አውስተዋል።

እንዲያውም ሥራው ተጀምሮ ውጤቱ ሳይታወቅ፦” የነዳጅ ማጣሪያው የት ሥፍራ መሆን አለበት?” በማለት የተወዛገቡ የክልል መስተዳድሮች መኖራቸውን የጠቆሙት ፀሀፊው፤ ከዚያ ሁሉ በሁዋላ ሥራው ውጤት አልባ በመሆኑ ኩባንያው ሥራውን አቋርጦ መውጣቱን ተናግረዋል።

“ ኩባንያው ጥሎ ከወጣ በኋላ እንኳን ነዳጁ ተደብቋል የሚሉ አልታጡም”ሲሉ አክለዋል አቶ ክንፈ ኪሩቤል።

 

የፔትሮናስ ኩባንያን ሥራ እንደ አብነት የጠቀሱት ፀሀፊው፤ ኩባንያው እጅግ ከፍተኛ የሪስክ ካፒታል ወጪ በመመደብ የነዳጅ ክምችት ይገኝበታል በሚባለው ሥፍራ  ከከርሰ ምድር ጥናት ጀምሮ –  የማግኔቲክና የድምጽ ሞገድ መረጃዎችን እስከመሰብሰብ ድረስ ያሉትንና   የነዳጅ ግኝት እንዳለ ለማረጋገጥ የሚያስችሉትን ሥራዎች በሙሉ  በከፍተኛ ወጪ  ቢያካሂድም፤ አንዲት ጠብታ እንኳ  እንዳለ የሚያመላክት ውጤት ሊያገኝ ባለመቻሉ የጋምቤላ የነዳጅ ፍለጋው  በኪሳራ መጠናቀቁን አትተዋል።

ፔትሮናስ፤  በጋምቤላ ጉድጓዶችን ብቻ ለመቆፈር ከ780 ሚሊዮን ብር  በላይ ለሌሎች የሰርቬይ ሥራዎች ደግሞ ወደ 130 ሚሊዮን ብር ማውጣቱን አቶ ክንፈ አመልክተዋል።

“ይህ ያልተሳካለት የነዳጅ ፈላጊ ኩባንያ ወደ ሶማሌ ክልል ዘልቆ በገናሌ ወንዝ እና በዋቤ ሸበሌ ወንዝ አካባቢ ተመሳሳይ ቁፋሮ አከናውኖ ነበር”ያሉት ፀሀፊው፤” እዚያም የጋምቤላው ዓይነት ዕጣ ስለገጠመው በከፍተኛ ብስጭት ንብረቱን ሸክፎ ከኢትዮጵያ ወጥቷል”ብለዋል።

ከፔትሮናስ መውጣት በሁዋላም ሌሎች የውጪ ኩባንያዎች ሥራቸውን ትተው ለመውጣት እያሰላሰሉ እንደሆነ መወራቱን አቶ ክንፈ ገልጸዋል።

“የነዳጅ ፍለጋ ሥራ እንደዋዛ የሚወራ ጉዳይ አይደለም”ሲሉም ፀሀፊው የአቶ መለስን አነጋገር ከሙያ አንፃር ይተቻሉ።

 

“የነዳጅ ፍለጋ ሥራ በትንቢት አይመራም፤ እጅግ የተወሳሰበ የሥራ ሒደት አለው:: እንደ ባለሙያዎች አባባል፣ የቀለጠ አለት በሽፈነው ምድር ወይም በከርሰ ምድር ሙቀትና ግፊት በተለወጠ ሥፍራ ነዳጅ አይገኝም::የካርቦንና የኃይድሮጂን ንጥረ ነገር የሚያመነጩ ተፈጥሯዊ ቅሪት አካላቶች በምድሩ ከሌሉ ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት

ለቀማ›› ነው ይላሉ ሳይንቲስቶቹ:: ይህም ሆኖ ነዳጅ አመንጪ አለቶች ካሉ በብዙ ሚሊዮን ዘመናት በከርሰ ምድር ሙቀት ተቀቅለው፣ ዘይት አመንጭተው ቀጥሎም

ወደ ማከማቻ ድንጋይ ቀዳዳ ገብተው እንዳይሸሹ- በተፈጥሮ ድንጋይ ተከድነው በጥልቅና በድቅድቅ ጨለማ የሚኖሩ ምትሐታዊ ፈሳሾች ናቸው” በማለት።

 

 

የዘርፉን ባለሙያዎች ጠቅሰው አቶ ክንፈ እንዳሉት፦ “ ያለ ብርሃን ዕርዳታ በድቅድቅ ጨለማ ክፍል ውስጥ፤ በአንዲት ጥግ የተደበቀን ዕቃ ለማግኘት እንደማይቻል ሁሉ፤ የነዳጅ ዘይትን ለማግኘት የስበትን፣ የማግኔትንና የድምፅን ባህርያት አቀናጅቶ የሚጠቀም የረቀቀ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ መጠቀም የግድ ነው።

“እንዲህም ሆኖ የማይሳካበት ሁኔታ አለ፤ የሰው ጥበብ የተወሰነ ነውና” ያሉት ፀሀፊው፤ በአገራችን እንኳንስ ነዳጅ ዘይት ቀርቶ ፦ውኃ ያለበትን ሥፍራ ለማወቅ ሳይንሱ

እየተፈታተነን ይመስለኛል”ብለዋል።

የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትሯ በበኩላቸው ሰሞኑን በፓርላማ ሪፖርት ሲያቀርቡ፤

“ የነዳጅ ዘይት ግኝት የሚረጋገጠው ነዳጁ ተቆፍሮ ሲወጣ ብቻ ነው” በማለት  ተናግረዋል።

ሚኒስትሯ አክለውም፦” ለዚያውም ክምችቱ ለኮሜርሻል (ለንግድ) አቅርቦት በሚበቃ መልኩ በተጨባጭ ሲገኝ ብቻ ነው መናገር የሚቻለው”ብለዋል።

የሚኒስትሯን አባባል ትክክለኛነት እንደሚጋሩት አቶ ክንፈ ተናግረዋል።

አቶ መለስ፤  በዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ በኢትዮጵያ ነዳጅ እንደሚገኝ መናገራቸውን ተከትሎ   የአገር ቤቶቹ  ሚዲያዎች  ልክ ነዳጅ እንደተገኘ  ወሬውን በስፋት መቀባበላቸው  እንዳሣሰባቸው የጠቀሱት አቶ ክንፈ፤ ገና ምኑም ባልተጨበጠ ሁኔታ  እንዲያ ብሎ መናገሩ ጉዳት እንጂ አንዳችም ጥቅም እንደሌለው አመልክተዋል።

ፀሀፊው  በመጨረሻም፦”ሲገኝ ብንናገር፤ ሥንሠራ ዝም ብንል ይጠቅማል እንጂ ጉዳት የለውም:: ቃል ተገብቶ ባይሳካ ተዓማኒነትን ማጣትና ዋሾ መባልን ያተርፋል”በማለት መለስን ሸንቁጠዋቸዋል።

አቶ መለስ በዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ ኢትዮጵያ በቅርቡ የነዳጅ ሀብት ባለቤት እንደምትሆን የተናገሩት ምን ጥቅም ወይም ትርፍ ለማግኘት ይሆን? የሚለው፤ ከዘርፉ ባለሙያዎች ባሻገር በርካታ አገሮችን ጭምር ያነጋገረ ሆኗል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide