ኢሳት (መስከረም 12 ፥ 2009)
በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመታዊ ጉባዔ ላይ በመሳተፍ ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ የማህበራዊ ድረገጾች በሃገሪቱ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው ሲሉ ቅሬታን አቀረቡ።
በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ መንግስት በማህበራዊ ድረገጾች አጠቃቀም ዙሪያ አጨቃጫቂ ነው የተባለ መመሪያ ተግባራዊ መደረጉ ይታወሳል።
በዚሁ የማህበራዊ ድረገጾች ዙሪያ በጉባዔው ንግግርን ያደረጉት አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ድርጊቱ የተለያዩ አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች መቻቻል እንዳይኖራቸው እያደረገ ነው ሲሉ ቅሬታን ማቅረባቸውን የተባበሩት መንግስታት የዜና ማዕከል ሃሙስ ዘግቧል።
ይሁንና አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ያጸደቀው አዲስ ህግ የማህበራዊ ድረገጽ አጠቃቀምን ለማፈንና ቁጥጥሩን ለማጠናከር ያለመ እንደሆነ ሲገልፅ ቆይተዋል።
በተባበሩት መንግስታት አመታዊ ጉባዔ ላይ ንግግርን ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ድረገጾች የሚያመጡት ተጽዕኖ ችላ ሊባል የሚገባው ጉዳይ አይደለም ሲሉ በንግግራቸው መሃል ማንሳታቸው የዜና አውታሩ በዘገባው አስፍሯል።
መንግስት ባለፈው አመቱ ያጸደቀው አዲሱ የማህበራዊ ድረገጾች አዋጅ በማንኛውም ሰው በኢንተርኔት አጠቃቀም ላይ የሚያደረገው የመረጃ ልውውጥ ክትትል እንዲደረግባት ይደነግጋል።
በዚህ ህግ መሰረት የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ለአመጽ የሚያነሳሱ ጽሁፎችን ወይም የቪዲዮ ምስሎችን አሰራጭተዋል ተብለው የተገኙ ሰዎች እስከ አምስት አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ይደነግጋል።
ይሁንና የሰብዓዊ መብት ተማኡጋች ተቋማትና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች አዲሱ አዋጅ የሃገሪቱ ሰዎች ለዜጎች መረጃን በነጻነት እንዲያገኙ የሚከለክል ነው በማለት መንግስት በአዋጁ ላይ ማሻሻያን እንዲያደርግ ዘመቻን እያካሄዱ ይገኛል።
በሃገሪቱ የነጻነት ሚዲያ በአግባቡ ባለመኖሩ ምክንያት በርካታ ሰዎች ፊታቸውን ወደ ማህበራዊ ድረገጾች ቢያዞሩም፣ የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ አማራጭ የመረጃ ምንጭ ላይ ጠንካራ እርምጃን እየወሰደ እንደሚገኝ እነዚሁ ተቋማት በመግለጽ ላይ ናቸው።