አቶ ሃብታሙ አያሌው በድጋሚ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠው

ሐምሌ  ፳፮ ( ሀያ ስድስት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በከፍተኛ ህመም የሚሰቃየው  አቶ ሃብታሙ አያሌው በአገር ውስጥ ሕክምና ሊድን እንደማይችል በሐኪሞች ቦርድ የተፈረመ ማስረጃ እንዲያቀርብ ተጠይቆ ቢያቀርብም፣  ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የጤናውን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት አፋጣኝ የሆነ የፍርድ ብያኔ ከመስጠት ይልቅ በተንዛዛ የጊዜ ቀጠሮ ውሳኔ መስጠት አልቻለም።

የሃብታሙን ጉዳይ ሲያዩ የነበሩ ሁለት ዳኞች በሌሎች ዳኞች መቀየራቸውን ጠቅላይ ፈርድ ቤቱ በምክንያትነት በመጥቀስ ፣ ጉዳዩን ለማየት ለሃምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም በድጋሚ ተጨማሪ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተዋል። የመሃል ዳኛ ከድር አልይን በዳኛ ሽመክት አሰፋ፣ የቀኝ ዳኛ ገበየሁ ፈለቀ  በዳኛ ፀሐይ መንክር ተተክተዋል።

”ዳኛ በማቀያየርና በማስቀረት በሞትና በሕይወት መካከል ባለች ነፍስ ላይ መቀለድ ምን አይነት ጭካኔ እንደሆነ፣ ምን የሚሉት ፍርድ እንደሆነ የሚገልጽልኝ ቃላት አጣሁ!” ሲል አቶ ዳንኤል ሺበሺ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አስመልክቶ የተሰማቸውን ቅሬታ በፌስቡክ ገጹ ላይ አስሯል።