ጥቅምት ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከአቶ መለስ ዜናዊ ዜና እረፍት ጋር ተያያዞ በባለሀብቶች በኩል በታየው አለመረጋጋት የተነሳ የዶላር እጥረት መከሰቱ፣ አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴው መዳከሙንና በአንጻሩም የአገሪቱ ኢኮኖሚ አደጋ ውስጥ መግባቱ ያሳሰበው የአቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ መንግስት የፊታችን ረቡዕ ጥቅምት 14 ቀን 2005 ዓም ከባላሀብቶች ጋር እንደሚወያዩ ታውቋል።
አቶ ሀይለማርያም ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር መካሄዱን በመግለጽ እስካሁን ድረስ ያልተረጋጉትን ባለሀብቶች ለማረጋጋት ይሞክራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ስብሰባው ሚካሄደው በእንዱስትሩ ልማት ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር ሲሆን፣ ስብሰባውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ከአቶ መኮንን ማን ያዘዋል ጋር ሆነው እንደሚመሩት ታውቋል።
ባለሀብቶች በበኩላቸው በውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ በባንክ ብድር፣ በመሬት፣ በአስተዳዳርና በተለይም ከቻይናና ከሌሎችም አገሮች በሚመጡ እርካሽ የውጭ እቃዎች ዙሪያ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጥያቄዎችን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አቶ ሀይለማርያም በቅርቡ ባደረጉት የፓርላማ ንግግር ባለሀብቶች አለመረጋጋት ይፈጠራል በሚል ተደናግጠው የውጭ አገር ገንዘቦችን ከባንኮች በአንድ ጊዜ ለማውጣት ተገደው እንደነበር መግለጻቸው ይታወሳል።