አትሌት ሙሉጌታ ዘውዴ በከፍተኛ ችግርና በህመም ላይ እንደሚገኝ ገለጸ።

መስከረም ፭ (አምስት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ከሁለት ዓመታት በፊት በኖርዌይ በተደረገ ተደጋጋሚ  የማራቶን ሩጫ ኢትዮጵያን ወክሎ በመወዳደር አንደኛ የወጣውና የአሸናፊነት ገመዱን

ሲበጥስ ሁለት እጆቹን ወደ ላይ በማጣመር የተቃውሞ ምልክት ያሳየው አትሌት ሙሉጌታ ዘውዴ በክፍተኛ ችግርና በህመም ላይ እንደሚገኝ ገለጸ።

በኖርዌይ በስደት የሚገኘው አትሌት ሙሉጌታ ለሁለት ጊዜ በተደረገ የማራቶን ውድድር ነበር ሁለት ጊዜ የኢሳትን ቲሸርት ለብሶ በመሮጥ ያሸነፈው።

ውድድሩንም ከማሸነፉ ባሻገር  በማጠናቀቂያው መስመር ላይ እጆቹን ወደ ላይ በማጣመርና የኢትዮጵያን መንግስት በመቃወም በነጻነት ትግሉ ላይ ችቦ የለኮሰ ፈር ቀዳጅ አትሌት

ነው-ሙሉጌታ።

አትሌት ሙሉጌታ ከኢሳት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ  በአትሌቲክሱ ዘርፍ እሱ የለኮሰው ችቦ እነ ፈይሳ ሌሊሳ ተረክበው በሪዮ ኦሎምፒክ ከፍ አድርጎ ሲያበሩት መመልከቱ ልዩ ደስታን

እንደሰጠው ተናግሯል። ይሁንና ይህ የትግል ቀንዲል  የሆነው አትሌት ዛሬ በከፋ ችግር ውስጥ ይገኛል።

አትሌቱ እንደገለጸው  ከሰራው ልምምድ ጋር በተያያዘ ለልብ ህመም መጋለጡ በሀኪም ቢነገረውም በቂ ህክምና ሊያገኝ አልቻለም።

እንዲሁም ደጋፍና በቂ ህክምና ሊያገኝ ባለመቻሉ ሳቢያ የመጣውን ለመቀበል በመፍቀድ ወደ ሀገሩ እንዲልኩት የኖርዌይን መንግስት እስከመጠየቅ መድረሱን የገለጸው አትሌት ሙሉጌታ፤

ሆኖም የኢትዮጵያ መንግስት “አትሌቱ አሸባሪ ስለሆነ አልቀበልም” የሚል ምላሽ መስጠቱን  ጠቅሷል።

ይህ ሁሉ ቢሆንም የኖርዌይ መንግስት የመኖሪያ ፈቃድ ሊሰጠው አልቻለም።

ጠበቃ በማቆም ያደረገው ክርክርም ውጤት ሊያሥገኝለት እንዳልቻለ ያመለከተው ሙሉጌታ፤ ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ በሚችሉት ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉለት ተማጽኗል።