ኢሳት (ታህሳስ 20 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በስፖርት ውድድር ወቅት አበረታች መድሃኒት ተጠቅመው የተገኙ አትሌቶች ዕድሜ ልክ ከውድድር እንዲታገዱ ያስተላለፈው ውሳኔ በአትሌቶች ዘንድ ተቃውሞ አስነሳ።
የፌዴሬሽኑ አዲሱ ፕሬዚደንት አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ፣ አበረታች ነው የተባለ መድሃኒት ተጠቅመው የተገኙ አትሌቶች ከእንግዲህ በኋላ የእድሜ ልክ እገዳ ይጣልባቸዋል ሲል ከሮይተርስ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ገልጸዋል።
ከወራት በፊት ስድስት የኢትዮጵያ አትሌቶች ውድድር ወቅት አበረታች መድሃኒት ተጠቅመው ተገኝተዋል ተብለው ምርመራ እየተካሄደባቸው የሚገኝ ሲሆን፣ የዕድሜ ልክ እገዳው እነዚሁኑ አትሌቶች ሊነካ እንደሚችል ተመልክቷል።
የአለም አቀፍ የኦሎምፒክ ኮሚቴ በውድድር ወቅት አበረታች መድሃኒት የተጠቀሙ አትሌቶች ለአራት ተከታታይ አመታት ከማንኛውም አለም አቀፍ ውድድር እንዲታገዱ ተግባራዊ ያደረገው ህግ ያመለክታል።
ይሁንና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ በድርጊቱ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ አትሌቶች ሃገራቸውን ዕድሜ ልክ ወክለው መወዳደር እንዳማይችሉ ለሮይተርስ አስረድተዋል።
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አትሌቶች በበኩላቸው አንዳንድ መድሃኒቶች በስህተት የሚወሰዱበት አጋጣሚ በመኖሩ ፌዴሬሽኑ ከማንኛውም ሃገር በተለየ መልኩ የወሰደው ውሳኔ በአትሌቶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው አስታውቀዋል።
ከውድድር በፊት ለተለያዩ የህመም ማስታገሻነት የሚወሰዱ መድሃኒቶች እንደ አበረታች ንጥር ነገር የሚወሰዱ በመሆኑ ድርጊቱ ከግምት ውስጥ መግባት እንደሚኖርበት አሳስበዋል።
አበረታች መድሃኒቶችን ሆን ብለው በስህተት በሚወስዱ አትሌቶች ላይ ምንም አይነት ልዩነት ሳይደረግ ተጠቃሚ ሆኖ የተገኘ አትሌት ያለምንም ምህረት እድሜ ልክ ከውድድር መታገዱ አግባብ አይደለም ሲሉ አትሌቶቹ ገልጸዋል።
የአለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና አለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በድርጊቱ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ አትሌቶች የሚተላለፍባቸውን የአራት አመት ዕገዳ ከመጠናቀቁ በኋላ ኦሎምፒክን ጨምሮ በማንኛውም አለም አቀፍ ውድድር መሳተፍ እንደሚችሉ ይደነግጋል።
በርካታ የኬንያ፣ የሞሮኮ፣ ዩክሬን፣ እና ቤላሩስ አትሌቶች ከስድስት ኢትዮጵያውያን ጋር ምርመራ እየተካሄደባቸው ሲሆን፣ ሩሲያ በሃገር ደረጃ ለአትሌቶቿ አበረታች መድሃኒትን ሰጥታለች ተብሎ ከአለም አቀፍ ውድድር ታግዳ ትገኛለች።