ኢሳት (ግንቦት 3 ፥ 2008)
መቀመጫውን በብሪታኒያ ያደረገና በቅርቡ በኢንቨስትመንት ስራ ላይ ለመሰማራት ወደ ኢትዮጵያ የገባ አንድ አለም አቀፍ ኩባንያ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ካለው የባንክ ሂሳብ (አካውንት) ውስጥ 2.4 ሚሊዮን ዶላር በመንግስት ተወስዶብኛል ሲል ሃሙስ ቅሬታን አቀረበ።
አትላስ አፍሪካን ኢንዱስትሪስ ሊሚትድ የተሰኘው ይኸው ኩባንያ በመንግስት ተወስዶብኛል ያለውን ገንዘብ ለማስመለስ ህጋዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ እንዲሁም ፖለቲካዊ አማራጮችን እየተመለከተ እንደሆነም ይፋ አድርጓል።
ይኸው በቅርቡ በብርጭቆና ጠርሙስ ምርቶች ላይ ለመሰማራት ወደ ሃገሪቱ የገባው ኩባንያ ከአንድ ሃገር በቀል ተቋም ጋር በሽርክና በመሆን ለራያ ቢራ ፋብሪካ ጠርሙሶችን ማምረት እንደ ጀመረ ገልጿል።
ይሁንና፣ ኩባንያው በሽርክና እየሰራ ያለው እና ቲፕ በሚል ምህጻረ-ቃል የሚጠራ ሃገር በቀል ኩባንያ አርዳን ከተሰኘ ድርጅት ከታክስ ጋር በተገናኘ ቅሬታ ቀርቦበት እንደነበር አስታውቋል።
አትላስ አፍሪካን ኢንዱስትሪስ የተሰኘው ተቋም ሽርክና ከመግባቱ በፊት በሁለቱ ኩባንያዎች የታክስ ጥያቄ በባለስልጣኑ መስሪያ ቤት መነሳቱን አውስቶ የታክሱ ጥያቄ ግን ኩባንያውን እንደማይመለከተው በመግለጫው አመልክቷል።
ይሁንና፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንን የተደረሱ ስምምነቶችን በመጣስ አትላስ አፍሪካ ኢንዱስትሪንና ቲፕ የተሰኘውን ሃገር በቀል ድርጅት በጋራ ተጠያቂ ማድረጉን ኩባንያው ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ ገልጿል።
ይህንንም ተከትሎ የገቢዎችና ጉምሩክ ባንክ በቅርቡ ከአትላስ ኩባንያ አካውንት 2.4 ሚሊዮን ዶላር ማውጣታቸውንና ድርጊቱም ህግን የጣሰ ተግባር እንደሆነ ኩባንያው አስታውቋል።
ይኸው መቀመጫውን በብሪታኒያ ያደረገውን በተለያዩ የቢዝነስ ስራዎች ላይ ተመስርቶ የሚገኘው ኩባንያ ከሃገር-በቀሉ ድርጅት ጋር ሽርክና ከመጀመሩ በፊት ድርጅቱ ያሉበት ጥያቄዎች እሱን እንደማይመለክቱት ህጋዊ ምክርን ማግኘቱን አስውቷል።
በመንግስት ያለ አግባብ ተወስዶብኛል ያለውን ገንዘብ አስመልክቶም ኩባንያው ለባለድርሻ አካላት ማብራሪያ የሰጠ ሲሆን፣ እርምጃውም ከጉምሩክ ባለስልጣን ጋር የተደረሰን ስምምነት የጣሰ ተግባር እንደሆነ ተመልክቷል።
100 ሚልዮን ብር አካባቢ የሚደርሰው ገንዘብ ለማስመለስም አትላስ አፍሪካ ኢንዱስትሪስ ሊሚትድ ኩባንያ ህጋዊ ዲፕሎማሲያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ አማራጮችን እየተመለከተ እንደሆነ ይፋ አድርጓል።
ኩባንያው በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ሊወስድ ያሰበውን እርምጃ በተመለከተም በቅርቡ መረጃዎችን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጿል።
የኩባንያው አቤቱታ በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት የሰጠው ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ ኩባንያው በአሁኑ ወቅት ለራያ ቢራ ፋብሪካ ጠርሙሶችን እያመረተ እንደሚገኝም የኩባንያው የበላይ ተጠባባቂ ሃላፊ የሆኑት ካርል ኤስፕሬይ በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸውን ከኩባንያው ድረ-ገጽ ለመረዳት ተችሏል።