አብዲ ኢሌ እየተገበረው ያለው ፖሊሲ በህወሃቱ ተወልደ በርሄ የተቀረጸ ነው ተባለ

አብዲ ኢሌ እየተገበረው ያለው ፖሊሲ በህወሃቱ ተወልደ በርሄ የተቀረጸ ነው ተባለ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 27 ቀን 2010 ዓ/ም) የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ ኢሌ በክልሉ የሚፈጽመው የሰብአዊ መብትም ጥሰትም ይሁን የሌሎች አካባቢ ተዋላጆችን የማፈናቀል ስራ በህወሃቱ ተወልደ በርሄ የተቀረጸው ፖሊሲ ውጤት መሆኑን ከህወሃት ጋር በተለያዩ የሃላፊነት ስራ የሰሩና አቶ አብዲ አሌን የአነሳስ ታሪክ የሚያውቁ ግለሰቦች ለኢሳት ገልጸዋል።
ምንጮች እንደገለጹት በ2 ሺ ዓም በታደሰ ካሳ በተሰራው የአመራር ምደባ ዛሬ የመለስ አካዳሚ ም/ዳይሬክተር የሆነው ተወልደ በርሄ ወደ ሶማሊ ክልል በመሄድ ሶህዴፓን እንዲያጠናክር ታዞ ለ3 ዓመታት ያክል በመቆየት የተሰጠውን ተልዕኮ በመጨረሽ ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል። ተወልደ የተሰጠው ተልዕኮ ከመብራት ሃይል ሰራ የተመለመለውን አቶ አብዲ ኢሌን ወደ ስልጣን ማምጣት ሲሆን፣ አቶ አብዲ አሌ በመጀመሪያ በቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አጠገብ በሚገኘውና አብዛኛው ታጋይ መሰረታዊ ትምህርት ወይም ማንበብና መጻፍ በሚማርበት የጎልማሶች ትምህርት ቤት እንዲገባ ከተደረገ በሁዋላ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለብቻው እየጠሩ በጽ/ቤታቸው ተጨማሪ ስልጠና ይሰጡት ነበር። ሲቪል ሰርቪስ ገብቶ በድጋፍ ትምህርቱን እንዲያጠናቅቅ የተደረገው አቶ አብዲ አሌ ፣ ትምህርቱን ሲጨርስ የሶማሊ ክልል የጸጥታ ጉዳዮች ሃላፊ ሆኖ መሾሙንና ህወሃትም እሱን ፊት በማድረግ የክልሉን ፖሊስና ሚሊሺ ማቋቋሙን እንዲሁም በሰብዓዊ መብቶች ረገጣ የሚወነጀለውን ልዩ ሃይል አቋቁሞለታል።
አሁን እያስፈጸመ ላለው ልዩ ተልዕኮ በማዘጋጀት አቶ አብዲ አሌ ወደ ፕሬዚዳንትነት እንዲመጣ የተደረገ ሲሆን፣ በክልሉ የሚካሄደውን ማንኛውንም እንቅስቃሴ ተወልደ ከጀርባ ሆኖ ክልሉን ይመራ እንደነበር የህወሃት ምንጮች ይገልጻሉ።
በ2009 ዓም ከጥቅምት 21-24 በተካሄደው የክልሉ ጉበኤ ከሁሉም የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ተወካዮች የተገኙ ሲሆን ኢህአዴግን በመወከል ጉባኤው ከተጠናቀቀ በሁዋላ ሁሉም ወደ መጠቡት አካባቢ ሲመለሱ አቶ ተወልደ ለተጨማሪ አንድ ሳምንት ጅግጅጋ በመቆየት በጉባኤው የተመረጠውን ስራ አስፈጻሚ ሰብስቦ የተለያዩ ትልዕኮዎችን አስጨብጧቸዋል። ከ2009 ዓም ጀምሮ በኦሮሞና በሌሎችን ብሄሮች ላይ የተደረገው መፈናቀልም ሆነ በህዝቡ ላይ የደረሰው ጉዳት በህወሃቱ አቶ ተወልደ ተደርሶ በአቶ አብዲ አሌ አስፈጻሚነት ተግባራዊ የሆነ ነው ሲሉ ምንጮች ገልጸዋል።
የክልሉን የልማትና የስራ ማስኪያጃ ገንዘብ የሚጠቀሙበት የእኛ ጓደኞች የሆኑ የህወሃት አመራሮች መሆናቸውን የሚገልጹት ምንጮች፣ አንዳንዶችንም ለአብነት ያነሳሉ። ፣የቀድሞው የደቡብ ምስራቅ እዝ አዛዥ አሁን የማእከላዊ እዝ አዛዥ የሆነውና የሶማሊ ክልል ባለሀብት ከሆነቸው ወ/ሮ ሃዋ ጋር በጋብቻ የተጣመረው ጄ/ል ዮሃንስ ወ/ጊዮርጊስ ፣ በእርሱ እና በባለቤቱ ስም ከመዘበረው የክልሉ ገንዘብ በተጨማሪ ቴዲ ማንጁስ ለተባለው የጄኔራሉ ዘመድ በክልሉ ባጀት ዘመናዊ የማስታወቂያና ህትመት ድርጅት ተከፍቶለት ፣ የክልሉን ህትመት ያለተወዳዳሪ እንዲወስድ ተደርጎ በአጭር ጊዜ ሚሊየነር ለመሆኑን መቻሉን ምንጮች ጠቅሰዋል።
የመለስ ዜናዊ ልጅ የሆነችው ሰመሃል መለስ እና የሃየሎም አርአያ ልጅ በ2008 ዓም ከፕሬዚዳንት አብዲ ኢሌ ገጸ በረከት የተበረከተላቸው ሲሆን፣ ገጸ በረከቱም ለእያንዳንዳቸው 1 ሚሊዮን 500 ሺ ብር እንደነበር በወቅቱ አብረዋቸው የተገኙት የህወሃት የአመራር አባላት ገልጸዋል።
ዳዊት ከበደ የተባለው የአውራምባ ታይመስ ገጽ ባለቤት፣ ስለ ሶማሊ ክልል በሰራው ለእያንዳንዱ ቪዲዮ እንደ ይዘቱ ከ85 ሺ እስከ 100 ሺ ብር ከክልሉ የልማት ባጀት ተነስቶ ሲከፈለው ሰናይት መብርሃቱ የምትባል የበለጸገች ኢትዮጵያ ገጽ ባለቤት፣ ቢኒያም ከበደ የተባለው የኢትዮ-ፈርስት እንዲሁም ኢ ኤን ኤን ቲቪ ጋዜጠኞች ለአንድ ጊዜ ብቻ ስለ ክልሉ ፕሮፓጋንዳ በሰሩ ቁጥር በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ብር ማበረታታቻ እየተባለ ይከፈላቸዋል።
አብዛኞቹ የህወሃት ባለስልጣናት አዲስ አበባ እና በተለያዩ ክልሎች የገነቡዋቸውን ቤቶች የሚያስጨርሱት ለሶማሊ ክልል ህዝብ ተብሎ ከሚመደበው በጀት መሆኑን ምንጮች ይገልጻሉ። አቶ አብዲ ኢሌ ክልሉ በከፍተኛ የምግብ እና የውሃ ችግር ተጠቅቶ በነበረበት ወቅት፣ ከአማራ ክልል ተፈናቀሉ ለተባሉ የትግራይ ተወላጆች 10 ሚሊዮን ብር መለገሱ ይታወቃል።