(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 11/2010) አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ መስመርን ማጠናከርና ማስቀጠል አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን የኢሕአዴግ ስራአስፈጻሚ ገለጸ።
የኢህአዴግ ስራአስፈጻሚ ለ8 ቀናት ያካሄደውን የስራ አስፈጻሚ ግምገማ አጠናቆ የድርጅቱን አጠቃላይ የምክርቤት ስብሰባ ጀምሯል።
ስራአስፈጻሚው ስብሰባውን ሲያጠናቀቅ ባወጣው መግለጫ እንዳለው ታዲያ በአመራሩ መካከል የነበረው የአመለካከት ልዩነት ወደ ተሻለ አንድነት እንዲመጣ አቅጣጫ ተቀምጧል።
የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመርን በሚያጠናከር መልኩ በአመራሩ መካከል የአመለካከት አንድነት በተሻለ ሁኔታ ተፈጥሮ መጠናቀቁን ድርጅቱ ገልጿል።
ስራ አስፈጻሚው እንዳለው አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመርን ማጠናከርና ማስቀጠል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። እናም መላው የኢህአዴግ አመራርና አባላት ይህንኑ መስመር መሰርት በማድረግ በጽናት ሊታገሉ እንደሚገባ ነው ያሳሰበው።
ከመጋቢት 2 እስከ መጋቢት 10 / 2010 ዓም ሲካሄድ የቆየው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ በብሄራዊ ድርጅቶች መካከል የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር የአመለካከት አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ በጥልቀት ተፈትሾ በመግባባት ተጠናቋል ነው ያለው መግለጫው።
የአራቱንም ብሄራዊ ድርጅቶች የስራ አስፈጻሚ እና የማዕከላዊ ኮሚቴዎች ግምገማ ሪፖርቶች በዝርዝር በመመልከትም በአሁኑ ወቅት እያጋጠሙ ያሉ የአመራር ችግሮችን ለማረም የሚያስችል የአመለካከት አንድነት ፈጥሪያለሁም ብሏል።
በዚህ ግምገማ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እያንዳንዳቸው ብሄራዊ ድርጅቶች በሂደት ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች በሚመርዋቸው ክልሎች እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ያላቸውን አስተዋጽኦ ተመልክቶ ጉድለቶች በፍጥነት እንዲታረሙ አቅጣጫ ማስቀመጡም ተመልክቷል።
ግንባሩና እያንዳንዱ ብሄራዊ ድርጅት ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመርና ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ከጥቃት ለመከላከል የህዝብን ጥያቄ በአግባቡና በፍጥነት መመለስ እንደሚያስፈልግም ተረድቻለሁ ብሏል።
የስራአስፈጻሚ ስብሰባውን መጠናቀቅ ተከትሎም የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።
በዚሁም የድርጅቱን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ምርጫውም በኢህአዴግ ፕሮግራም፣ ህገ ደንብና በተለመደው የኢህአዴግ አሰራር መሰረት እንደሚከናወን በመግለጫው ተመልክቷል።