(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 10/2010) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ ስራዬን ለመስራት ተቸግሬያለሁ በማለት ስልጣን ለመልቀቅ መናገራቸውን የቤተክህነት ምንጮችን ዋቢ ያደረጉ መረጃዎች አመለከቱ።
ሐራ ተዋህዶ የተባለው በቤተክርስቲያኒቱ ጉዳይ ላይ የሚያተኩረው ድረገጽ እንደዘገበው ፓትሪያርኩ ሃላፊነታቸውን ለመልቀቅ በቃል ያሳወቁ ሲሆን በቀጣይም በጽሁፍ ያሳውቃሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ባለፉት 4 ቀናት በአዲስ አበባ በተካሄደው የቤተክርስቲያኒቱ 36ኛ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ በዋሽንግተን የሚገኙትን አቡነ ፋኑኤልን ፓትሪያርኩ መወረፋቸው ይፋ ሆኗል።
ላለፉት አምስት አመታት ያህል በፓርትሪያርክነት መንበር ላይ የተቀመጡት አቡነ ማትያስ በዙሪያቸው በከበቧቸው የሕወሃት አባላት በሆኑ ካህናት ግፊትና ተጽእኖ ከሌሎች አባቶች ጋር እየተጋጩ ከቤተክርስቲያኒቱ ልዩ ልዩ ማህበራት ጋር እየተወዛገቡ መቀጠላቸው ሲነገር ቆይቷል።
አሁንም ከቤተክርስቲያኒቱ አባቶችና በቤተክርስቲያኒቱ ስር ከሚንቀሳቀሱ ማህበራት ጋር በፈጠሩት ውዝግብ ተግባብተው መስራት እንደተሳናቸው ተገልጿል።
ከዚሁ ጋር በተያይዘ አቡነ ማትያስ ስልጣናቸውን ሊለቁ እንደሚችሉ በቃል መናገራቸውም ይፋ የሆነው በዚሁ ሳምንት መሆኑን የሀራ ተዋህዶ ዘገባ አመልክቷል።
እንደዘገባው ከሆነ በቃል ያቀረቡትን መልቀቂያ በቅርቡ በጽሑፍ ያቀርባሉ ተብሎም ይጠበቃል።
በቀጠዩ ሰኞ የሚጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤም በአቡነ ማትያስ ቅሬታና ተቃውሞ ዙሪያ ይነጋገራል ተብሎ ይጠበቃል።–የመንግስትም ጣልቃ ገብነት ሊኖር ይችላል ተብሏል።
በቤተክርስቲያኒቱ ሕግ አንድ ፓትሪያርክ ስልጣኑን የሚያጣው ሀይማኖታዊ ስህተት ሲፈጽም አልያም ታማኝነቱንናን መንፈሳዊ አባትነቱ ተቀባይነትን ያጣ ከሆነና ይህም በተጨባጭ ተረጋግጦ በቅዱስ ሲኖዶስ ሲወሰን እንደሆነ በሕገ ቤተክርስቲያን ተደንግጓል።
እንደከዚህ ቀደሙ መንግስት ጣልቃ ገብቶ ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዎስን እንዳነሳው በዚህም ላይ የራሱን ተጽእኖ ካላደረገ ፓትሪያርኩ ስልጣን መልቀቅ የሚችሉበት ሁኔታ አይኖርም።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በዋሽንግተንና አካባቢዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጳጳስ የሆኑት አቡነ ፋኑኤል ጵጵስናውን ያገኙት በገንዘብ ሃይል መሆኑን ፓትሪያርኩ በአደባባይ ተናግረዋል።
አቡነ ማትያስ ይህንን የተናገሩት ለአራት ቀናት ተካሂዶ በተጠናቀቀው 36ኛው የሰበካ ጉባኤ መንፈሳዊ ስብሰባ ላይ ሲሆን ይህም በምስልና በድምጽ ተሰራጭቷል።
አቡነ ፋኑኤል ስልጣን ላይ ያለውን የኢህአዴግ መንግስት አውግዘው በአሜሪካ ጥገኝነት ጠይቀው የአሜሪካ ዜግነት ከወሰዱ በኋላ ኢትዮጵያ ተመልሰው ሔደው በአቡነ ጳውሎስ የተሾሙ ጳጳስ መሆናቸው ይታወቃል።