አበረታች መድሃኒት በሚወስዱ አትሌቶች ላይ የእድሜ ልክ እገዳ ለመጣል የተወሰደው ዕርምጃ አለም አቀፍ ተሞክሮን ያካተተ እንዲሆን አሰልጣኞች ጠየቁ

ኢሳት (ታህሳስ 27 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አበረታች መድሃኒት ተጠቅመው በሚገኙ አትሌቶች ላይ የእድሜ ልክ እገዳ ለመጣል የወሰደው ዕርምጃ አለም አቀፍ ተሞክሮን ያካተተ እንዲሆን አሰልጣኞች ጠየቁ።

በቅርቡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚደንት ሆኖ የተመረጠው አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ አበረታች መድሃኒት ተጠቅመው የተገኙ የሃገሪቱ አትሌቶች ዕድሜ ልክ ከእስፖርቱ እንዲታገዱ እንደሚደረግ ከቀናት በፊት ለሮይተርስ መግለጹ ይታወሳል።

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አትሌቶች ዕርምጃው አበረታች መድሃኒትን ባለማወቅ የሚወስዱ አትሌቶችን በጅምላ ይጎዳል ሲሉ ለኢሳት ቅሬታን አቅርበዋል።

በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ስጋታቸውን መግለጽ የጀመሩ አሰልጣኞችና ሌሎች አካላት ፌዴሬሽኑ ተግባራዊ አደርገዋለሁ ያለውን የእገዳ እርምጃ በአለም አቀፍ ጸረ-አበረታች መድሃኒት ኤጀንሲ መሰረት ቢሆን የተሻለ ነው ሲሉ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አሰልጣኝ ሁሴን ሸቦ ውሳኔው በተለይ በጉዳዩ ዙሪያ በቂ መረጃ የሌላቸውን አዳዲስ አትሌቶች ሊጎዳ እንደሚችል ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

አበረታች መድሃኒት ተጠቅመው የሚገኙ አትሌቶች ላይ የሚወሰደው ዕርምጃም በአለም አቀፍ ጸረ አበረታች መድሃኒት ኤጀንሲ መሰረት መሆን አለበት ያሉት አሰልጣኙ መድሃኒቶቹ ያለማወቅ የሚወሰዱበት አጋጣሚም መኖሩን ጠቁመዋል።

አበረታች መድሃኒት ወስደው ተገኝተዋል የተባሉት አትሌቶች ለተከታታይ ሶስት አመታት እገዳ እንደሚጣልባቸው የአለም አቀፉ ጸረ-አበረታች መድሃኒት ኤጀንሲ ደንግጓል።

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው የእድሜ ልክ እገዳ ኢትዮጵያ አበረታች መድሃኒት ለሚጠቀሙ አትሌቶች ምህረት እንዳማይኖራት ለማሳየት ነው ሲል አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ ለሮይተርስ አስረድቷል።

ይኸው ዕርምጃ ኢትዮጵያ በአትሌቶች ላይ ዕድሜ ልክ ዕገዳን ስትጥል ብቸኛ ሃገር የሚያደርጋት ሲሆን፣ አትሌቶችና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ደንቡ በተለይ በጀማሪ አትሌቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳትን እንደሚያስከትል አሳስበዋል።

በአለም አቀፍ ደረጃ የሚወዳደሩ አትሌቶች አበረታች መድሃኒቶችን ያለማወቅ የሚወስዱበት አጋጣሚ በመኖሩ ጉዳይ መጤን ይኖርበታል ሲሉ ባለሙያዎቹ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ስድስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አበረታች መድሃኒት ተጠቅማችኋል ተብለው በአለም አቀፍ ደረጃ ምርመራ እየተካሄደባቸው ሲሆኑ አትሌቶቹ በምርመራው ጥፋተኛ ከተባሉ የእድሜ ልክ ዕገዳው ተግባራዊ ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። ወደ 200 የሚጠጉ አትሌቶች በተያዘው አመት ምርመራ ይካሄድባቸዋል ሲል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።