ሐምሌ ፲፱ ( አሥራ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኦፌኮ ም/ል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ የቀረበባቸው የሽብር ወንጀል ክስ ተቀይሮና በወ/ህ ቁጥር 257/ሀ መሰረት እንዲከላከሉ ፍርድ ቤት የወሰነላቸው መሆኑን ተከትሎ፣ አንቀጹ የዋስትና መብት የማያስከለክል በመሆኑ የዋስ መብታቸው እንዲከበርላቸው ቢያመለክቱም፣ አቃቢ ህግ ተቃውሞ አቅርቧል።
አቃቢ ህግ “ ይህ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ማየት ሲጀምር በህግ አግባብ ተከሳሹን የዋስትና መብት ከልክሎ በማረሚያ ቤት ሆኖ ይህ ጉዳይ እልባት እስኪያገኝ ጉዳዩን እንዲከታተል ትእዛዝ ሰጥቷል።
ይህ ጉዳይ የመጨረሻ እልባት የሚያገኘው ደግሞ የመጨረሻው የፍርድ ውሳኔ ሲሰጥ ነው። አሁን ተከሳሽ አንቀጽ ተቀይሮ ተከላከል መባሉ ለጉዳዩ እልባት አሰጥቷል የሚያስብል አይደለም።
በዚህም ምክንያት የዋስትናው ጉዳይ ላይ ይሄ ፍርድ ቤት ትእዛዝ የሰጠበት ጉዳይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በድጋሜ ጉዳዩን ይሄው ፍ/ቤት ተመልክቶ ትእዛዝ ሊሰጥ የሚችልበት ህጋዊ ምክንያት የለም።” ብሎአል።
አቃቢ ህግ አክሎም ተከሳሹ ተከላከል የተባለበት የወ/ህ ድንጋጌ የዋስትና መብትን ባያስከለክልም ተከሳሹ ግንኙነት ሲያደርግ የነበረው ውጪ ከሚገኙ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ጋር በመሆኑ እና እሱም ከአገር የሚወጣበት አጋጣሚ በመኖሩ የዋስትና መብቱ ቢጠበቅለት ግዴታውን አክብሮ ይቀርባል የማያስብል ነው ብሏል:: አያይዞም ተከሳሹ ፈጽሞታል በሚል ክስ ከቀረበበት ድርጊት አንጻር እና ተከላከል ሲባል ከፈጸመው ግዙፋዊ በሆነ ሁኔታ የማነሳሳት ተግባሩ በዋስትና ቢወጣ በተመሳሳይ ተግባር ለይ ሊሳተፍ እና ሌላ ወንጀል ሊፈጸም የሚችል በመሆኑ በወ/መ ቁጥር 67 መሰረት ዋስትናው ተከልክሎ በማረሚያ ቤት ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል ይታዘዝልን ብሎአል።
ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ እልባት ለመስጠት ለሃምሌ 26 ቀን 2009 ዓም ቀጠሮ ሰጥቷል።