አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መደንገጉን ተከትሎ በየቀኑ  በኦሮሚያ ክልል  በወጣቶችና ምሁራን ላይ ዘግናኝ የሆነ ስቃይ ሲፈጸም መቆዬቱን  የአፍሪቃ ቀንድ የሰብዓዊ መብት ሊግ አጋለጠ።

ታኅሣሥስ ፫ (ሦስት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የሰብዓዊ መብት ሊጉ” ስድሳ እኩይ ቀናት በኦሮሚያ”በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ  መደንገጉን ተከትሎ  ባለፉት ስድሳ ቀናት እጅግ በርካታ  የኦሮሞ ወጣቶች፣  የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ፣ የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ምሁራን ላይ ያነጣጠረ  አፈናና ጥቃት ሲፈጸም መቆዬቱን አመልክቷል።

የህወኃት ኢሃዴግ አገዛዝ በሰብዓዊ ነት ላይ እየፈጸመ ያለውን ግፍ በሪፖርተሮቹ አማካይነት ሲያጠናቅር መቆዬቱን የጠቀሰው የሰብ ዓዊ መብት ሊጉ፣ የተፈጸሙትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች  ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ ማጋለጡን እንደሚቀጥል አስታውቋል።

እንደ ቀንዱ ሰብዓዊ መብት ሊግ መግለጫ -እስካሁን በተሰባሰቡት ሪፖርቶች መሰረት አጋዚ የተሰኘው የህወኃት ኢህአዴግ  ገዳይ ቡድን  በየቀኑ እስራትን፣ግድያን፣ አስገድዶ መድፈርንና  አፍኖ መሰወርን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነቶች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸሙ ተመልክቷል።

ነቀምቴ ከሚገኘው የቅወለጋ ዩኒቨርሲቲ በታህሣስ የመጀመሪያው ሳምንት ታፍነው ከተወሰዱት ስምንት ተማሪዎች መካከል የአራተኛ ዓመት የሲቪል ኢንጂነሪንግ ተማሪ የሆነው  ሳቦና ቻልሺሳ፣ የሁለተኛ ዓመት  የሲቪል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ከራጅ ሞቲማ እና ከሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ  የተወሰደው የሁለተኛ ዓመት የአካውንቲንግ ተማሪ ናቡሊ ምስጋና ወርቅነህ  ይገኙበታል።

በተመሳሳይ፡መንገድ  በደቡብ መእራብ ሸዋ ዞን ከቱሉ ቦሎ  የህብረት ትምህርት ቤት የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት  መምህር አበበ አንጋሳ በታህሳስ ወር መጀመርቲያ ላይ ታፍነው  መወሰዳቸው በመግለጫው ተጠቅሷል።

የሰብአዊ መብት ሊጉ በደቡብ ኦሮሚያ በባሌ ዞን  በአዳባ ቀጣና ከሚገኙት ከጋዴዶ ማህበረሰብ አባላትና  ከዳራባ ከተማ  ነዋሪዎች መረጃዎችን ማሰባሰቡን የጠቀሰው መግለጫው፣ መረጃዎቹ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር  ታህሳስ 6 ዕለት ምሽት ላይ  በርካታ የአካባቢዎቹ ወጣቶችና ምሁራን ታፍነው ወደማይታወቅ ስፍራ  መወሰዳቸውን የሚያመለክቱ እንደሆኑ ገልጿል።

የአፍሪካ ቀንድ የስብዓዊ መብት ሊጉ ለኢሳት በላከው በዚሁ መግለጫ  በህወሀት ኢህአዴግ አፋኝ ኃይሎች ከአዳባ ታፍነው የተወሰዱትን 12 ሰዎች ፣ እንዲሁም ከጉጂ ዞን  ከሳባ ቦሩ ታፍነው የተወሰዱትን 16  ሰዎች  ስም ዝርዝር ከነ አድራሻቸው ይፋ አድርጓል።

ህወኃት ኢህ አዴህ – የኦሮሚያ ክልልን  ያለማቋረጥ በየዕለቱ  ወደ ሀዘን ለውጦታል የሚለው የሰብ ዓዊ መብት ሊጉ፤ “ዜጎች በየዕለቱ እያነቡና እያለቀሱ ቢሆንም ማንም ሊደርስላቸው አልቻለም። በአካባቢው ምን እየተፈጸመ እንደሚገኝ ግንዛቤው ያለውም ዓለማቀፉ ማህበረሰብም ቢሆን”ብሏል።

ዓለማቀፉ ህብረተሰብ  በእንዲህ ያሉ ጉዳዩች ዙሪያ  እርምጃ ወስዶ ድርጊቱን ከማስቆም  ይልቅ በዝምታ ድባብ የተዋጠበት  ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የሊጉ መግለጫ ያትታል። “ ዓላማቀፉ ማህበረሰብ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ እንዲገባ ምን ያህል ሰዎች  መጨፍጨፍ አለባችው?” በማለትም ይጠይቃል  የስብዓዊ መብት ሊጉ።

መግለጫው በመጨረሻም በክልሉ እየተፈጸመ ያለው ነገር የሰብ ዓዊ መብት ሊጉን እጅግ እንዳሣሰበው በመጥቀስ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ በህወኃት ኢህ አዴግ አምባገነን መንግስት ላይ ተጨባጭ እርምጃ በመውሰድ ለኦሮሞ ህዝብ ያለውን አጋርነት ያረጋግጥ ዘንድ ጥሪ አቅርቧል።

ይህን መግለጫም  ለበርካታ አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ ተቋማትና ድርጅቶች ልኳል።