ኢሳት (ሚያዚያ 5 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ በመባባስ ላይ ባለው አዲስ የድርቅ አደጋ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ የሚፈልጉ ወረዳዎች ቁጥር ወደ 364 ማሻቀቡ ተገለጠ።
ሲጠበቅ የነበረው የበልግ ዝናብ በሚፈለገው መጠን ባለመጣሉ ምክንያት 5.6 ሚሊዮን የሆነው የተረጂዎች ቁጥር በቀጣዮቹ ጥቂት ወራቶች እንደሚጨምር የአደጋ መከላከልና አስተዳደር ኮሚሽን ማስታወቁን የቱርኩ ዜና አገልግሎት አናዱሉ ዘግቧል።
ከአንድ ወር በፊት በድርቁ የተጎዱ ወረዳዎች ቁጥር ወደ 240 አካባቢ እንደነበር ይፋ ተደርጎ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የወረዳዎቹ ቁጥር 364 መድረሱ ተመልክቷል።
ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ መገኘት የነበረበት ድጋፍ ባለመገኘቱ ድርቁ እየተባባሰ እንዲሄድ ተጨማሪ ምክንያት መሆኑንም ታውቋል።
የኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ወደ ስድስት ሚሊዮን ከሚሆኑ ተረጂዎች መካከል ሁለት ሚሊዮን የሚሆነውን ድርሻ የያዘ ሲሆን፣ በክልሉ ከድርቁ ጋር ተያይዞ በተከሰተ የኮሌራ ወረርሽኝ ሰዎች በመሞት ላይ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ዋቢ በማድረግ ረቡዕ መዘገባችን ይታወሳል። የአደጋ መከላከልና አስተዳደር ኮሚሽን ሃላፊ የሆኑት አቶ ምትኩ ካሳ ድርቁን ለመከላከል ከቀረበው አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ አብዛኛው ሊገኝ አለመቻሉን ለቱርኩ የዜና አገልግሎት አስረድተዋል።
በድርቁ ምክንያት የተከሰተው የምግብ እጥረት በተጨማሪ የበሽታዎች ወረርሽን ስጋት ሆኖ የቀጠለ ሲሆን፣ 4.4 ሚሊዮን ሰዎች የጤና እንክብካቤን እንደሚፈልጉ ኮሚሽኑ ገልጿል።
በአፋር፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ የሚገኙ በርካታ ዞኖች አዲስ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሆነ አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች አስታውቀዋል።
የመንግስት ባለስልጣናት የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ቢያረጋግጡም ትክክለኛ ቁጥሩን ግን ከመግለፅ ተቆጥበዋል።
ይሁንና የተረጂዎቹ ቁጥር ይፋ ከመደረጉ በፊት ጉዳዩ የሚከታተላቸው አካላት በጉዳዩ ዙሪያ እንደሚመክሩበት የአደጋ መከላከል እና አስተዳደር ኮሚሽን በቅርቡ መገልፁ ይታወሳል።
ከአንድ አመት በፊት 10 ሚሊዮን ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ለአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ መጋለጥ ምክንያት የነበረው ተመሳሳይ የድርቅ አደጋ ሙሉ ለሙሉ ሳይቀረፍ አዲስ አደጋ መከሰቱ በሰብዓዊ ዕርዳታ ስራው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩም ተመልክቷል።
በአራት ክልሎች ጉዳትን እያደረሰ ያለው የድርቅ አደጋ እስከቀጣዩ አመት ድረስ ቀጣይ ሊሆን እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት አሳስቧል።
የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው በምግብ እጥረት የሰው ህይወት እንዳይጠፋ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን በመግለጽ ላይ ናቸው።
ይሁን እንጂ የእርዳታ ድርጅቶች በቀጣዮቹ ሁለትና ሶስት ወራት ችግሩ ከተጠበቀው በላይ ጉዳትን ሊያስከትል እንደሚችል በማሳሰብ ላይ ናቸው።