ኢሳት (የካቲት 17, 2008)
በኢትዮጵያ በስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለውን የድርቅ አደጋ ተከትሎ አስቸኳይ የምግብ እንክብካቤን የሚፈልጉ ህጻናት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት አስታወቀ።
በድርቁ ሳቢያ እርዳታን ይፈልጉ የነበሩ የአምስት ሚሊዮን ህጻናት ቁጥርም ወደስድስት ሚሊዮን ያደገ ሲሆን ድርቁ በመባባስ ላይ መሆኑንም ድርጅቱ ገልጿል።
አስቸኳይ የምግብ ድጋፍን ከሚፈልጉት ስድስት ሚሊዮን ህጻናት መካከልም ከ430ሺ በላይ የሚሆኑት ልዩ የነብስ-አድን የምግብ እንክብካቤን የሚፈልጉ መሆናቸውን ዩኒሴፍ አመልክቷል።
ለተረጂዎች የሚሆን የምግብ አቅርቦት በወቅቱ ባለመድረሱም የህጻናቱ ህይወት አደጋ ላይ ወድቆ መገኘቱንም የህጻናት መርጃ ድርጅቱ በድርቁ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርቱ ገልጿል።
በስድስት ክልሎች በሚገኙ ከ180 በላይ ወረዳዎች ውስጥ ተከስቶ ያለው ይኸው የድርቅ አደጋ በህጻናት ተማሪዎች ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት እየጨመረ በመምጣቱም ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ህጻናት በመጨመር ላይ መሆኑም ታውቋል።
በአሁኑ ወቅትም በድርቁ ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች የተዘጉ ሲሆን ወደሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናትም ትምህርት ማቋረጣቸውን የህጻናት መርጃ ድርጅቱ አመልክቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ወደሃገሪቱ መግባት ካልጀመረ ከ10 ሚልዮን የሚበልጡ ተረጂዎች ከቀጣዩ ወር ጀምሮ የሚቀርብላቸው የምግብ አቅርቦት እንደማይኖር ሰሞኑን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
አለም-አቀፍ ተቋማቱ ድርቁ አስቸኳይ ርብርብ ካልተደረገለት ወደረሃብ ሊለወጥ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩንም ገልጸዋል።
ይሁንና፣ በኢትዮጵያ ድርቀን ተከትሎ ረሃብ የሚመጣበት ዘመን አልፏል ሲል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ምላሽን ሰጥቷል።
ሃገሪቱ ከሚያስፈልጋት ከ 1.4 ቢሊዮን የእርዳታ አቅርቦት ውስጥ እስከአሁን ድረስ ከግማሽ በታች የሚሆነው ብቻ መገኘቱንና የአቅርቦት ክፍተት ማጋጠሙን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አክሎ አመልክቷል።
መንግስት በበኩሉ በሃገሪቱ ታሪክ ከባድ ድርቅ ማጋጠሙን በመግለፅ ድርቁ ግን ወደረሃብ አይቀየርም በማለት የአለም አቀፍ ድርጅቶችን ማሳሰቢያ አስተባብሏል።