ግንቦት ፩ ( አንድ ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሳምንታዊው ካፒታል እንደዘገበው ከፍተኛ መጠን ያለው ይህ የተፈጬ በርበሬ ከአውሮፓ ገበያ ሊመለስ የቻለው፤ በአውሮፓ መግቢያ ባሉ ላቦራቶሪዎች በተደረገ ምርመራና ቁጥጥር አፍላቶክሲን እና ኦክራቶክሲን የተባሉ በካይ ንጥረ ነገሮች ስለተገኙበት ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ በርበሬው የተቀመጠውን የጥራት ደረጃ እስካላሟላ ድረስ ወደ ለንደን እንዳይገባ ባለፈው ዓመት የእንግሊዝ መንግስት እገዳ መጣሉ ይታወሳል። ይህም በመሆኑ በለንደን ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጥራቱን ለማሻሻል ከበርበሬ ላኪዎች ጋር መሥራት እንደጀመረ ተገልጿል።
ጀርመን በበኩላ ከፍተኛ መጠን ያለው የኢትዮጵያ በርበሬ ወደ ግዛቷ እንዳይገባ ማገዷ ይታወቃል። የበርበሬ ላኪዎቹ ለካፒታል እንደተናገሩት ካለፈው ዓመት ወዲህ እጅግ በጣም ከፍተኛ መጠን ያለው በርበሬከዋና ገበያቸው ከአውሮፓ መግቢያ ተመልሶባቸዋል።
በመሆኑም በዓመት እስከ 9 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ያስገኝ የነበረው የበርበሬ የውጪ ንግድ ክፉኛ መጎዳቱን አቶ አዲሲ ዓለማዬሁ የተባሉ የዘርፉ ተመራማሪ ገልጸዋል።