ጥቅምት ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢሳት የአርባምንጭ ምንጮች እንደተናገሩት በቅርቡ የአርበኞች ግንቦት 7 ደጋፊዎች ኢህአዴግን የሚያወግዙና ወጣቱ ለመብቱ እንዲነሳ የሚቀሰቅሱ በራሪ ወረቀቶችን ከበተኑ በሁዋላ፣ ድርጊቱን ፈጽመዋል ብለው የጠረጠሩዋቸውን ወጣቶች በጅምላ ለማሰር ከትናንት ጀምሮ አሰሳ አካሂደዋል።
አሰሳውን ተከትሎ የ70 አመት አዛውንት እናትን ጨምሮ ሴቶችና ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ወጣቶች ተይዘዋል። ከተያዙት መካከል የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪ እንደሚገኙበት ምንጮች ገልጸዋል። አቶ ሉሉ መሰለ እስከ ባለቤታቸውና ልጃቸው ተይዘው፣ ልጃቸውና ባለቤታቸው ሲለቀቁ እርሳቸው ታስረዋል፡፤ ቀደም ብሎ ቂልንጦ ተወስዶ የታሰረው የአቶ ፈቃዱ አበበ እናት ወ/ሮ አልማዝ ካሳና እህቱ አየለች አበበም እንዲሁ ” ተፈላጊ ልጃቸውን ባንተወሰን አበበን አምጡ” ተብለው ታስረዋል።
ወጣት ባንተወሰን አበበ ፣ በአጋጣሚ ቤት ውስጥ ባለማደሩ አለመያዙንና እናትና እህቱን አስረው መውሰዳቸውን እንዲሁም ከቤታቸው ተገኝቷል የተባለ መረጃ ፈርሙ ተብላ እህቱ ስትጠየቅ አልፈርምም ማለቱዋን ለኢሳት ገልጿል።