አርበኞች ግንቦት7 በአዲ ጎሹ ፣ ቃፍታ ሁመራ አካባቢዎች ውጊያ ማካሄዱን አስታወቀ

ኅዳር ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ከድርጅቱ ወታደራዊ ክፍል የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ባለፉት ሳምንታት የድርጅቱ ታጣቂዎች በቃፍታ ሁመራ፣ አዲ ጎሹና አርማጭሆ አካባቢዎች ከህወሃት/ኢህአዴግ ቃኝ ወታደሮች ጋር ተከታታይ የተኩስ ልውውጦችን አድርገዋል።በተኩስ ለውውጡ ከመንግስት በኩል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች ሙት እና ቁስለኛ ቢሆንም፣ ከነጻነት ሃይሎች በኩል የደረሰውን ጉዳት ለማወቅ ድርጅቱ ምርመራ እያደረ መሆኑን ገልጿል።

“የንቅናቄው ሃይሎች አንዳንድ ቦታዎችን ተቆጣጥረዋል እየተባለ ነው ፣ ይህ ልክ ነው ወይ?” የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አንድ የንቅናቄው የወታደራዊ አመራር አባል ሲመልሱ ፣ “ የማናካሂደው ጦርነት የሽምቅ ውጊያ ነው፣ ወደ ተለያዩ ቦታዎች በምናደርገው እንቅስቃሴ ከጠላት ቃኝ ሃይል ጋር ፊት ለፊት እንጋጠማለን፣ እኛ ተዘጋጅተን ስለምንሄድባቸው ብዙ ጊዜ የበላይነት እንይዛለን፣ በጊዜያዊነት የምንይዛቸው ቦታዎች ሊኖሩም ይችላሉ” ብለዋል።

“እኛ የምንፈጽማቸውን ጥቃቶችም ሆነ የምናደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ለደህንነት ሲባል ይፋ አናደርጋቸውም “ የሚሉት የአመራር አባሉ፣ አገዛዙ ከእኛ በኩል መረጃ ማግኘት ባለመቻሉ መረጃዎችን ከተለያዩ ሚዲያዎች እየሰበሰበ ለመተንተንና የእኛን አካሄድ ለማወቅ ሙከራ እያደረገ ነው” ብለዋል።

በመንግስት በኩል እስካሁን የተሰጠ መግለጫ የለም።