አርበኞች ግንቦት 7 ለጎንደር ህዝብ አጋርነቱን እየገለጸ እንደሚገኝ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ

ኢሳት (ሃምሌ 6 ፥ 2008)

አርበኞች ግንቦት 7 መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው የጎንደር ህዝብ አጋርነቱን እየገለጸ እንደሚገኝ ሊቀመንበሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ። የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በምስልና ድምፅ ከኤርትራ ረቡዕ ዕለት ባስተላለፉት መልዕክት የአማራም ህዝብ ሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አጋርነቱን እንዲያሳይ ጥሪ አቅርበዋል።

የወልቃይት ህዝብ ማንነቱን በተመለከተ በህጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ያቀረበው ጥያቄ በህወሃት በኩል የሃይል ምላሽ መሰጠቱ የቀሰቀሰው ተቃውሞ ወደግጭት ማምራቱን በጥሪያቸው ያስታወሱት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ በጎንደር የታየው ህዝባዊ ዕምቢተኝነት በስርዓቱ ሰለባ ለሆኑትና ለውጥ ለሚሹ ሁሉ መነቃቃትን የፈጠረ እንደሆነ አመልክተዋል።

“ከተባበርን አንጸናለን፣ ከተከፋፈልን እንወድቃለን” በማለት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የአጋርነት ጥሪ ያቀረቡት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ “ዛሬ በጎንደር ከተማ እና አካባቢዋ እየተዋደቁ ካሉ ወገኖቻችን ጎን ካልቆም በህወሃት የሚደርስብን አፈና ማለቂያ አይኖረውም በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለመከላከያና ለፌዴራል ፖሊስ አባላት ለብዓዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴን እንዲሁም ለህወሃት አባላት ጭምር በገዳዮችና ዘራፊዎች ላይ ተነሱ በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

አገዛዙን በመቃወም የሚደረጉ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች የትግራይን ህዝብ ለማጥቃት የተካሄደ በማስመሰል የሚቀርበውን አሳፋሪ ሴራ እንዲያጋልጥም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኦሮሚያና የአማራ ክልል የፖሊስና የሚሊሺያ አባላት ለነበራችውና አሁንም ላላችሁ በጎ ሚና ህዝቡ አክብሮቱን ይሰጣችኋል በማለት ከኤርትራ በምስልና በድምፅ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከዚህ ውጭ በወንጀል ተባባሪ የሆኑና በግድያ ተሳታፊ የሆኑ የጸጥታ ሃይሎች በማናቸውም መንገድ ከተጠያቂነት ነጻ እንደማይሆኑ አሳስበዋል።

“በአንድነት ከተነሳት የነጻነት ቀን ቀርባለች” በማለት ወደንግግራቸው ማጠቃለያ የመሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ በሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች የአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮች እንደሚገኙ አመልክተው፣ “ስትሞቱ እየሞትን ስትቆስሉ እየቆሰልን፣ ሊገድሏችሁ ያኮበኮቡትን እየታገልን እስከመጨረሻው የድል ምዕራፍ ከውስጣቸው እንደማንለይ ዕወቁት” ሲሉ መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።