ሰኔ 15 ፥ 2009
በሰሜን ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ በኮማንድ ፖስት ወታደሮች ለግድያ በመወሰድ ላይ የነበሩ ሁለት ወንድማማቾች የአርበኞች ግንቦት ሰባት ታጣቂዎች በወሰዱት እርምጃ ከግድያ ማምለጣቸው ታወቀ። ወንድማማቾቹ ትላንት ረቡዕ ለሃሙስ ሌሊት በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር 6 ሰዓት ላይ ወደ ሚገደሉበት ቦታ እየተወሰዱ በነበረ ጊዜ በመንገድ ላይ በተከፈተ ተኩስ ማምለጣቸው ታውቋል።
ገላጋይ ሲሳይ በቀለ እና አስማረ ሲሳይ የሚባሉት እነዚህ ወንድማማቾች በሰሜን ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ ነጋዴ ባህር በንግድ ስራ ይተዳደሩ ነበር። ሰኔ 14 2009 ዓመተ ምህረት ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ ሁለቱ ወንድማማቾች በኮማንድ ፖስቱ ቁጥጥር የዋሉት ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ጋር ትገናኛላችሁ በሚል እንደሆነ ተመልክቷል። ወንድማማቾቹ ለአርበኞች ግንቦት 7 ድጋፍም ታደርጋላችሁ እንደተባሉና በተለይም በአካባቢው በትግል ስም ከሚታወቀው አርበኛ ተፈሪ ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነት ደርሰንበታል የሚል ምክንያት ያቀረቡት የኮማንድ ፖስቱ ወታደሮች ድንገት ከመንገድ ላይ ይዘው መውሰዳቸው ተነግሯል። ከዚያ በኋላ የሆነው ለሁለቱ ወንድማማቾች ከባድ እንደነበር የገለጸው የኢሳት ምንጭ፣ በኮማንድ ፖስቱ ወታደሮች በዱላ መደብደባቸውንና ለሰዓታት በዘለቀ በዚህ ድብደባ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሏል።
ከዱላውና ድብደባው በኋላ ገላጋይና አስማረ ታስረው በመኪና ላይ ተጭነው ወደአልታወቀ ስፍራ በኮማንድ ፖስቱ ወታደሮች ሲወሰዱ በአካባቢው ለሚገኘው የግንቦት ሰባት ሃይል መረጃው እንደደረሰው ከስፍራው ያገኘነው ዜና ያመለክታል። ኢሳት ያነጋገረውና ለግድያ እየተወሰደ የነበረው ገላጋይ ሲሳይ በቀለ ሊረሽኗቸው እንደነበር ሆኖም ቀናቸው ስላልደረሰ ከሞት ማምለጣቸውን ተናግሯል። ሊያድኑን ለመጡት ሃይሎች ምስጋና ይድረሳቸው ሲል ለኢሳት ገልጿል።
የአርበኞች ግንቦት ሰባት የአካባቢው አዝማች አርበኛ ተፈሪ ለኢሳት እንደገለጸው ሁለቱ ወንድማማቾች ሊገደሉ እየተወሰዱ መሆኑ መረጃው እንደደረሳቸው በፍጥነት እርምጃ ለመውሰድ መንቀሳቀሳቸውን ተናግረዋል።
ገላጋይ ሲሳይና ወንድሙ ግድያ እንጂ እንተርፋለን የሚል ተስፋ እንዳልነበራቸው ሆኖም ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት በኮማንድ ፖስቱ አባላት ታጅበው እየተወሰዱ ባሉበት ሰዓት ድንገት የተኩስ ድምጽ ሲሰሙ ድንጋጤ ውስጥ መግባታቸውንና ተኩሱ እነሱን በጫነውና በኮማንድ ፖስቱ ወታደሮች በታጀበው ተሽከርካሪ ላይ ያነጣጠረ እንደነበር ተናግረዋል።
ወንድማማቾቹ ገላጋይና አስማረ በተኩስ ልውውጡ መሃል ወደ አገኙት አቅጣጫ ሮጠው መለያየታቸውንና ገላጋይ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ሃይሎች እጅ ሲገባ አስማረ ወደ ሌላ አከባቢ አምልጦ በኋላ ላይ ግን በስልክ መገናኘታቸውን ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።