አርበኛ መቶ አለቃ ደጀኔ በተኩስ ልውውጥ መሃል መሰዋቱ ታወቀ

ታኅሣሥ ፲፬ (አሥራ አራት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ታህሳስ 12 ቀን 2009 ዓም በነጻነት ሃይሎች እና በህወሃት/ኢህአዴግ ወታደሮች መካከል ቋራ ላይ ተደርጎ በነበረው ከባድ ውጊያ ከመንግስት በኩል ቁጥራቸው በውል ያልተወቀ ወታደሮች ሲገደሉ፣ ከነጻነት ሃይሎች መካካል ደግሞ መቶ አለቃ ደጀኔ መንግስቱ መስዋት መሆኑን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

አርበኞቹ እንደሚሉት  መቶ አለቃ ደጀኔ የኢትዮጵያ ህዝብ ያጣውን ነጻነት፣ ፍትህና ዲሞክራሲ አስመልሳለሁ በሚል ቤተሰቡን፣ ሃብትና ንብረቱን በመተው ትግሉን የተቀላቀለ ሲሆን፣ በቋራ በነበረው ግንባር ፊት መሪ ሆኖ ሲያዋጋ ውሎአል።

አርበኞች የያዙትን ቦታ ሳያስደፍሩ አዳዲስ ተመልምለው በተላኩ የስርዓቱ ወታደሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ገልጸው፣ መቶ አለቃ ደጀኔ አንድ ከባድ መሳሪያ የያዘ ወታደር አቁስሎ ካጠለው በሁዋላ የሞተ መስሎት መሳሪያውን ለመማረክ በሚሄድበት ወቅት ተመትቶ መውደቁን በቁጭት ገልጸዋል። በዚሁ ውጊያ ከአርበኛ ደጀኔ በቀር ሌላ ጉዳት የደረሰበት ታጋይ እንደሌለና ታጋዮቹም በሰላም ከአካባቢው መሰወራቸውን ገልጸዋል።

የመቶ አለቃ ደጀኔን አስከሬን በወታደራዊ ስነስርዓት መቅበራቸውን የገለጹት ታጋዮቹ፣ አካባቢውን ለቀው ከሄዱ በሁዋላ የገዢው ፓርቲ ወታደሮች ጋዜጠኛ ይዘው በመምጣት ቀረጻ አካሂደዋል ብለዋል። በሰሜን ጎንደር የነጻነት ታጋዮች ከስርዓቱ ወታደሮች ጋር የሚያደርጉት ውጊያ እንደቀጠለ ሲሆን፣ ገዢው ፓርቲም አካባቢውን ማረጋጋት እንደተሳነው የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በቋራ አካባቢ ስለተካሄደው ውጊያ ገዢው ፓርቲ እስካሁን የሰጠው መግለጫ የለም።