አራት ኢትዮጵያውያን በኬንያ የጸረ ሽብር ግብረሃይል ተያዙ

ጥር ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የምስራቅ አፍሪካ ሰብአዊ መብቶች ሊግ ለኢሳት በላከው መግለጫ  የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑት አራቱ ኢትዮጵያውያን በኬንያ የጸረ ሽብር ግብረሃይል የታየዙት በተለያዩ ቀናት ነው።

ቱምሳ ሮባ ካቲሶ የተያዘው ኢስሊ እየተባለ በሚጠራው የገበያ ስፍራ ሲሆን፣ በሁለት መኪኖች የመጡ የጸጥታ ሃይሎች በፈረንጆች አቆጣጠር ፌብሩዋሪ 1፣ አፍነው ወዳልታወቀ ስፍራ ወስደውታል።

ጫላ አብደላ፣ ናሚ አብደላ፣ እንዲሁም ስሙ በውል ያልታወቀው ሶስተኛው ሰው ደግሞ ፌብሩዋሪ ሶስት በተመሳሳይ ሰዎች ታፍነው ተወስደዋል።

ሊጉ ለኬንያ መንግስት በጻፈው ደብዳቤ፣ ኢትየጵያውያኑ ወደ አገራቸው ሳይላኩ አይቀርም ብሎአል። የኬንያ መንግስትም በአለማቀፍ ህግ መሰረት የሰዎችን አድራሻ ይፋ እንዲያደርግ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ደህንነቶች በቅርቡ 2 የኦጋዴን መሪዎችን ኬንያ ውስጥ አፍነው መውሰዳቸው ይታወቃል። ቢቢሲ ዛሬ ባወጣው ዘገባ ተደራዳሪዎችን አሳልፈው ሰጥተዋል የተባሉት የኬንያ ፖሊሶች ጥፋተኞች አለመሆናቸውን ገልጿል።

የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት የጸጥታ አማካሪ በበኩላቸው ባለስልጣኖቹ ታፍነው ሳይሆን ራሳቸውን ለመንግስት አሳልፈው መስጠታቸውን ተናግረዋል።