ነኅሴ ፳፮ (ሀያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም አስከባሪ ጦር አሚሶም ስር የዘመተው የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ሰራዊት በመሃከላዊ ሶማሊያ በገልጋዱ ግዛት ውስጥ አራት ንፁሃን የሶማሊያ ዜጎችን በግፍ መግደሉንና ከሟቾቹ ውስጥ ሁለቱ መምህራን መሆናቸው ተገልጿል።
”በአካባቢያችን በኢትዮጵያ ታጣቂዎች እንደዚህ ዓይነት አስቀያሚ እርምጃዎች እየተወሰዱብን እኛ ከዚህ በላይ ልንታገስ አይገባንም።ይቅርታ ልናደርግላቸውም አይገባንም።ካለርህራሄ አራት ንፁሃን ሰላማዊ ዜጎቻችንን ገለውብናል።” በማለት በአካባቢው ታዋቂ የአገር ሽማግሌ የሆኑት አሊ ፋራ ተናግረዋል።
አዛውንቱ “በአካባቢው አንድም የአልሸባብ ታጣቂዎች አልነበሩም።ከገደሏቸው በተጨማሪም አስራ አንድ ሶማሊያዊያንን ይዘው ወዳልታወቀ ስፍራ ሄደዋል።ይሄ የሚያሳያው ፀብ ጫሪነትን እንጂ ሰላም አስከባሪነትን አይደለም” ይላሉ።
የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ሰራዊት በማእከላዊ ሶማሊያ ግዛት ውስጥ ኢሰብዓዊ የሆኑ ግፎችን እየፈጸመ ሲሆን፣ ባለፈው ወር በሃልጋን ክልል ውስጥ በ አንድ ሚኒባስ ላይ በከፈቱት የእሩምታ ተኩስ ስምንት ንፁሃን ዜጎችን መግደላቸው ይታወሳል ሲል ማረግ ዘግቧል።
በተመሳሳይ ዜና በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም አስከባሪ ጦር ፣ በ ጃናሌ የጦር ካንፕ ላይ አልሸባብ በፈጸመው ጥቃት፣ ከሰባ በላይ የሰላም አስከባሪው ወታደሮች መገደላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በደቡባዊ ሶማሊያ የደረሰውን ፍንዳታ ተከትሎ ለሰዓታት የዘለቀ የተኩስ ልውውጥ ተደርጓል።የሰላም አስከባሪው ወታደሮች የጦር ምሽጋቸውን በመልቀቅ ሲሮጡ መታየታቸውን የቢቢሲ ሪፖርተር ጨምሮ ገልጿል። አሚሶም ግን የጦር ምሽጋችንን አለቀቅንም ሲሉ ማስተባበያ ሰጥቷል።