ኢሳት ( ግንቦት 1 ፥ 2008)
በማህበራዊ ድረ-ገጽ መንግስት በመተቸቱ ብቻ የታሰረው አቶ ዮናታን ተስፋዬና ሌሎች ያለምክንያት የታሰሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲቀቁ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ መንግስትን ጠየቀ።
አቶ ዮናታን ተስፋዬ ከማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ ተቃውሞና ከዚያ በኋላ የጸጥታ ሃይሎች በህዝቡ ላይ በወሰዱት መጠነ ሰፊ የሃይል እርምጃ ተከትሎ ፌስቡክ ላይ በጻፈው ትችት፣ ኢህአዴግ በሰላም ከመነጋገር ይልቅ ሃይል መጠቀሙ አግባብ እንዳልሆነ መግለጹ የሚያሳስረው አይደለም ሲል ይኸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የኢህአዴግን ድርጊት ኮንኗል።
የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሚያ የተከሰተው ተቃውሞ በኦነግ የተቀነባበረ ነው የኦነግን አላማ የሚያራምዱ ጽንፈኞች የቀሰቀሱት ተቃውሞ ነው ካለ በኋላ፣ አቶ ዮናታንም አመጽ በመቀስቀስ፣ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም ዝግጅት በማድረግ፣ የአገሪቷን የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ መረጋጋትን ለማወክ በማሴር በሚሉ 11 ክሶች መከሰሱም ታውቋል። በዚህም አቶ ዮናታን ከኦነግ ጋር በመተባበር፣ አመጹን በማቀጣጠል በሚሉ ተጨማሪ ክሶች መከሰሱ ተሰምቷል።
ባለፈው በታህሳስ ወር 2008 የታሰረው የሰማያዊ ፓርቲ ቃል አቀባይ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በዚሁ በውሸት ክስ የሞት ፍርድ ሊፈረድበት ይችላል ሲልም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ስጋቱን አክሎ ገልጿል።
ሆኖም የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪካ፣ የአፍሪካ ቀንድና የታላላቅ ሃይቆች አገሮች ዳይሬክተር የሆኑት ሙቶኒ ዋንየኪ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ሁሉ በሽብርተኝነት እንደሚወነጅልና አቶ ዮናታን በፌስቡክ የጻፈው በመሬት ወረራ ላይ ያተኮረ ትችትም ወንጀል እንዳልሆነና ይህ ተግባር በምንም መልኩ ሽብርተኝነት እንዳማያስብለው ተናግረዋል። የአቶ ዮናታን ተስፋዬ መታሰር የኢትዮጵያ መንግስት የተንጋደደውን የጸረ-ሽብርተኝነትን ህግ በመጠቀም የተቃዋሚ ሃይሎችን ዝም ለማሰኘት የሚጠቀምበት መሆኑን አመላካች ነው ሲሉ ሚስተር ዋይንኪ አክለው ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት አቶ ዮናታን ተስፋዬ በማዕከላዊ እስር እንዳለ ግፍ (ቶርቸር) እንዳልተፈጸመበት፣ ትክክለኛና ግልጽነት የተሞላበት ምርመራ እንዲያደርግ ጠይቋል።