አምነስቲ ኢንተርናሽናል በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለተከሰተው የህይወት መጥፋት አደጋ የኢትዮጵያ መንግስት ተጠያቂ ነው አለ

ኢሳት (መጋቢት 5 ፥2009)

በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከ60 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት ለሆነው አደጋ የኢትዮጵያ መንግስት ተጠያቂ ነው ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ መንግስት በርካታ ሰዎች በቆሻሻ ክምር አጠገብ ለብዙ ጊዜያት ሲኖሩ ዝም ብሎ መመልከቱንና አደጋው ቀድሞ ሲወሰድ በሚችል የጥንቃቄ እርምጃ መከላከል ይቻል እንደነበር ገልጿል። የአካባቢው ነዋሪዎች ለባዮ-ፊዩል የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክት ግንባታ በመካሄድ ላይ የነበረ ስራ ለቆሻሻ ክምር መደርመስ ምክንያት መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለደረሰው አደጋ ሙሉ ለሙሉ ሃላፊነትን ይወስዳል ሲል ያስታወቀው አምነስቲ ኢንተርናሽናል አደጋውን ቀድሞ መከላከል ይቻል እንደነበር በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

መንግስት የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታው ከአቅም በላይ መሙላቱን እያወቀ ቆሻሻ የማጠራቀሙ ሂደት እንዲቀጥል ማደረጉንም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ገልጿል።

በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ስፍራው ህይወታቸውን ለአደጋ በሚጥል ሁኔታ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች መንግስት መጠለያና የስራ ዕድልን ሊፈጥርላቸው ባለመቻሉ ለአስከፊው አደጋ መጋለጣቸውን አምነስቲ አስታውቋል።

ቅዳሜ ምሽት በደረሰው በዚሁ አደጋ ከ60 በላይ ሰዎች መሞታቸው ቢረጋገጥም አሁንም ድረስ የገቡበት ያልታወቁ ሰዎች መኖራቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አክሎ ገልጿል።

የደረሰው አሳዛኝ አደጋ አፋጣኝ የማጣራት ስራ እንዲካሄድበት ጥሪውን ያቀረበው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ለችግሩ ተጠያቂ የሚሆኑ ባለስልጣናት ለፍትህ መቅረብ እንዳለባቸው በተቋሙ የምስራቅ አፍሪካ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ ሃላፊ የሆኑት ሙቶኒ ዋንየኪ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ለአምነስት ኢንተርናሽናል አስቀድሞ ከአደጋው የተረፉ የአካባቢው ነዋሪዎች መንግስትን ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን፣ ለሃይል ማመንጫ ግንባታው ሲካሄድ የነበረ የመሬት መደልደል ስራ የቆሻሻ ክምሩ እንዲናድ ምክንያት መሆኑን ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ አስረድተዋል።

በርካታ ሰዎች በስፍራው እንደሚኖሩ እየታወቀ የከተማዋ አስተዳደር ለነዋሪዎቹ ማሳሰቢያን ሳይሰጥና እንዲነሱ ሳያደርግ ግንባታ ሊያካሄድ መቆየቱን ሃላፊነት የጎደለው ስራ መሆኑን እነዚሁ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

አደጋው በምሽት በመድረሱም የነፍስ አድን ሰራተኞች በቶሎ ሊደርሱ አለመቻላቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ሁኔታው የሟቾች ቁጥር እንዲበዛ አስተዋጽዖ ማድረጉንም ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአደጋው መድረስን ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪዎችን ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ ማድረጉ ታውቋል። ይሁንና አስተዳደሩ ዕርምጃን አስቀድሞ መውሰድ እንደነበረበትና የጠፋውን የሰው ህይወት ማዳን ይቻል እንደነበር የተለያዩ አካላት ገልጸዋል።

አደጋው በደረሰበት ስፍራ ለአራተኛ ቀን ፍለጋ ሲካሄድ መዋሉን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ የመለክታል።

የቤተሰብ አባሎቻቸውን ያጡ በርካታ ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ፍለጋው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥያቄን እያቀረቡ እንደሆነም ለመረዳት ተችሏል።