አሜሪካ የተመድ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ጸረ-እስራዔል አቋም ያራምዳል በማለት ከአባልነት ልትሰናበት ትችላለች ተባለ

ኢሳት (ግንቦት 29 ፥ 2009)

አሜሪካ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ጸረ-እስራዔል አቋምን ይዟል በማለት ከምክር ቤቱ አባልነት ልትሰናበት እንደምትችል ማክሰኞ አሳሰበች።

የምክር ቤቱ 47ኛ አባል ሃገራት በአለም ዙሪያ ስላሉ የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎች ላይ ለመምከር በስዊዘርላንድ መዲና ጄኔቭ የሁለት ሳምንት ጉባዔውን እንደጀመሩ ኢንዲፔንደንት ጋዜጣ ከስፍራው ዘግቧል። ሂውማን ራይትስ ዎች መካሄድ በጀመረው መድረክ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ አጀንዳ ሆኖ እንዲቀርብ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በተደጋጋሚ እስራዔልን በሚመለከት የሚያወጣቸው መግለጫዎች ጸረ-እስራዔል ዝንባሌ ያላቸው ናቸው ሲሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሃሊ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ አባል ሃገራት እስራዔል በመካከለኛው ምስራቅ እንደፈረጆቹ አቆጣጠር በ1967 አም የተካሄደውን ጦርነት ምክንያት በማድረግ አሁንም ድረስ የፍልስጥኤም መሬትን ይዛ ትገኛለች በማለት ሲያወግዙ ቆይተዋል።

ይሁንና የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ምክር ቤቱ በእስራዔል ላይ ያለውን አቋም መፈተሽ ይኖርበታል ሲል ቅሬታ ሲያቀርብ መሰንበቱ ይታወሳል።

ምክር ቤቱ ማክስኞ በጀመረው ጉባዔው ላይ የተገኙ አምባሳደር ኒኪ ሃሊ በሰብዓዊ መብት ጥሰታቸው የሚታወቁ ሃገራት በቂ ትኩረት ባልተሰጠባቸው ሁኔታ ድርጅቱ በእስራዔል ላይ ከወራት በፊት አምስት መግለጫ ማውጣቱን አውስተዋል።

የሰብዓዊ መብት ምክር ቤቱ በአቋሙ ላይ ማስተካከያ የማያደርግ ከሆነ ሃገራቸው ከአባልነቷ ልትሰናበት እንደምትችል አምባሳደር ማሳሰባቸውን ኢንዲፔንደንት ጋዜጣ በዘገባው አቅርቧል።

ሂውማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ 12 አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የምክር ቤቱ አባላት በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲወያዩ ደብዳቤ ማቅረባቸው ሲዘገብ ቆይቷል።

ምክር ቤቱ በተለይ በኦሮሚያ ክልል የተካሄደውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በሃገሪቱ የደረሰውን ጉዳት እና ግድያ ለመመርመር ጥያቄ ቢያቀርብም መንግስት ጥያቄውን ሳይቀበለው ቀርቷል።

መንግስታዊው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባካሄደው ምርመራ በሶስት ወራት ውስጥ ብቻ 699 ሰዎችን መገደላቸውን አስታውቋል።

ይሁንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ድርጊቱ በገለልተኛ አካል ማጣራት የተካሄደበት ባለመሆኑ ቁጥሩ ሊበልጥ ይችላል ሲሉ ምላሽን ሰጥተዋል። ምርመራን እንዲያካሄድ እገዳ የተጣለበት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ምርመራውን በድጋሚ ለማካሄድ ጥያቄን ቢያቀርብም ከመንግስት በኩል የተሰጠው ምላሽ የለም።

ምክር ቤቱ ማክሰኞ በጀመረው በዚሁ ጉባዔ በአለም ዙሪያ ስላሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ሰፊ ውይይትን ያካሄዳል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ አሳሳቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችም እንደሚተላለፍ ተመልክቷል።