ኢሳት (ታህሳስ 18 ፥ 2009)
ሩሲያ አሜሪካ የሶሪያ አማጺያን ቡድንን በዘመናዊ የጦር መሳሪያ ለማስታጠቅ የያዘችውን እቅድ ተቃወመች።
የፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር በቅርቡ ለሶሪያ አማጽያን ለማቅረብ የወሰነው የጦር መሳሪያ ድጋፍ በሶሪያ የሚገኙ ወታደሩን ደህንነት ስጋት ውስጥ ያካተተ ነው ስትል ሩሲያ ድርጊቱን ኮንናለች። አሜሪካ የባሽር አላሳድ መንግስት ለመጣል ለሚታገሉ ሃይሎች ጸረ አውሮፕላን ሚሳይሎችን ጨምሮ ሌሎች ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ድጋፍ ለማድረግ በቅርቡ መወሰኗ ተመልክቷል።
ይሁንና የሶሪያው ፕሬዚደንት ባሽር አላሳድ መንግስት የምትደግፈው ሩሲያ በሃገሪቱ የሚገኙ ወታደሮቿ በአማጽያኑ ጥቃት ኢላማ ሊሆኑ ይችላል የሚል ስጋት እንዳደረባት የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮባ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ሩሲያና አሜሪካ በሶሪያ እያደረጉ ያለው የተናጠል ድጋፍ አለመግባባት ውስጥ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ አሜሪካ ለሶሪያ አማጺያን የሚሰጡት የጦር መሳሪያ ማዕቀቦች እንዲነሱ ባለፈው ሳምንት መወሰኗን VOA እንግሊዝኛው ክፍል ዘግቧል።
የዚህኑ ማዕቀብ መነሳት ተከትሎ አሜሪካ ለአማጺ ቡድኑ ጸረ-አውሮፕላን ሚሳይሎችን ልትሰጥ እንደምትችል ተነግሯል።
ዕርምጃው ጸብ አጫሪነት ነው ስትል የገለጸችው ሩሲያ፣ ከዚህ በፊት ጥቃት ተፈጽሞበት የነበረው ኤምባሲዋ ጭምር ስጋት እንዳደረባት ገልጻለች።
የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮብ የሶሪያ መንግስት ከአማጺያን ጋር በካዛኪስታን ምክክር ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከሩሲያ ከፍተኛ ወታደራዊ ድጋፍ ሲደረግላቸው የነበሩት ፕሬዚደንት ባሸር አላሳድ ለአምስት አመት ያህል በአማጺያን ቁጥጥር ስር የነበረችውን የአሌፖ ከተማ ሙሉ ለሙሉ መልሰው ለመቆጣጠር መብቃታቸው ይታወቃል።
ይሁንና አሁንም ድረስ አላሳድ ከስልጣን እንዲወገዱ የሚታገሉ አማጺያን በተለያየ የሃገሪቱ ክልሎች የሚገኙ በመሆኑ ሶሪያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰላሟን ታገኛለች ተብሎ እንደማይገመት የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።
ሩሲያ ኢራን እና ቱሪክ አሜሪካንን ያላሳተፈ የሰላም ድርድር በሩሲያ መንግስትና በማጺያን በኩል እንዲካሄድ ጥረትን እያደረጉ ሲሆን፣ ድርጊቱ በአሜሪካ ዘንድ ስጋትን መፍጠሩ ተነግሯል።
ሩሲያ ባለፈው አመት በሶሪያ የወሰደችው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ እያሻከረ እንዲሄድ ምክንያት መሆኑን የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ሲሆኑ ሩሲያ በተመራጩ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ዘመን ግንኙነቱ ሊሻሻል እንደሚችል ተስፋ መኖሩን ገልጻለች።