(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 17/2010) አሜሪካ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ልታደርገው የነበረውን ውይይት መሰረዟን አስታወቀች።
ስለስብሰባው አስብበታለሁ ስትል የከረመችው ሰሜን ኮሪያ በበኩሏ በማንኛውም ሰአት ከአሜሪካ ጋር ውይይት ለማድረግ ፍላጎት አለኝ ስትል አስታውቃለች።
ደቡብ ኮሪያ አሜሪካ ታሪካዊ የተባለውን ይህንን ውይይት በመሰረዟ አዝኛለሁ ማለቷ ታውቋል።
ከቀናት በፊት ነበር ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር የታሰበውን ውይይት በአሜሪካ በኩል የአስገዳጅነት ስሜት ታይቷል በሚል ውይይቱን ልሰርዝ እችላለሁ ስትል ያስጠነቀቀችው።
ይህንን ተከትሎ ነው ታዲያ የአለምን ትኩረት ስቦ የነበረው የሰሜን ኮሪያና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የሰኔ ቀጠሮ የአሜሪካው ፕሬዝዳትን ዶናልድ ትራምፕ ቀጠሮውን ሰርዣለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ከወዲሁ ያበቃለት ይመስላል።
ታሪካዊ የሰላም ስምምነት ይሆናል በሚል ሲሞካሽ የነበረው የሁለቱ መሪዎች ቀነ ቀጠሮ ከወዲሁ እክል የገጠመው ታዲያ ከሰሜን ኮሪያ በኩል የሚወጡ መግለጫዎች ቁጣን ያዘሉ ናቸው።
ይህ በመሆኑ ደሞ ለውይይቱ ተነሳሽነትን አጥተናል ነው ያለው የፕሬዝዳንት ትራምፕ ደብዳቤ።
በዚህም የተነሳ ውይይቱን ለማካሄድ በአሜሪካ በኩል ፍላጎት አልመኖሩን ገልጸዋል።
አስቀድማ ውይይቱን ልሰርዝ እችላለሁ ስትል የቆየችው ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ አቋም በተቃራኒው በመቆም በማንኛውም ሰአት ውይይቱን ለማካሄድ ፍላጎት አለኝ ስትል ተደምጣለች።
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ሙን ጄ ኢን የሁለቱ ሃገራት ውይይት በዚህ መልኩ መሰናከሉ አሳዛኝና ያልተጠበቀ ክስተት ነው ብለውታል።
ተስፋ የተጥሎበት የነበረው የሁለቱ መሪዎች ውይይት ከወዲሁ ተሰርዟል መባሉ በሰሜን ኮሪያውያን ዘንድ ከፍተኛ ሀዘን መፍጠሩን ቢቢሲ ዘግቧል።
ይህ ዜና እየተጠናቀረ ባለበት በዚህ ሰአት ደግሞ ውይይቱን ሰርዤያለሁ ያሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ውይይቱ ሊቀጥል የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል ሲሉ መደመጣቸውን ዘገባው አመልክቷል።