አሜሪካ አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን ወደ አዲስ አበባ መላኳን አስታወቀች

ኢሳት (ጥር 10 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ ስላለው የፓለቲካ ሁኔታ ስጋቷን በመግለጽ ላይ የምትገኘው አሜሪካ አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን ወደ አዲስ አበባ መላኳን አስታወቀች።

ነገ ሃሙስ አዲስ አበባ የሚገቡት የሀገሪቱ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፌልድ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር በመገናኘት በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚመክሩ ይጠበቃል።

ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር የሚመክሩት ሚኒስትሯ አዲስ አበባ ከሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ሰራተኞች ጋርም በመገናኘት ተመሳሳይ ውይይትን እንደሚያካሄዱ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሃላፊዋን ጉብኝት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ አሜሪካ አዋጁ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት መባባስ ምክንያት ይሆናል በማለት ስጋቷን ስትገልጽ መቆየቷ ይታወሳል።

የአዋጁ መውጣት ምክንያት በማድረግ ከአንድ ወር በፊት የሃገሪቱ የሰብዓዊ መብቶችና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ሃላፊ በአዲስ አበባ የሶስት ቀን ቆይታን በማድረግ ለአስቸኳይ አዋጁና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ማካሄዳቸው አይዘነጋም።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዘጠኝ ወር የሚቆየውን ይህንኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መውጣት ተከትሎ ዜጎች ወደ ሃገሪቱ ቢጓጓዙ አደጋ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ማሳሰቢያን አውጥቶ ይገኛል።

በቅርቡ በጎንደርና ባህርዳር ከተሞች የደረሰውን የቦምብ አደጋ ተከትሎ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጎቹ ጥንቃቄን እንዲያደርጉ አሳስቧል።

አሜሪካ በተደጋጋሚ ስትሰጥ በቆየችው ማሳሰቢያ ቅሬታውን ሲገልጽ የቆየው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሃገሪቱ የወሰደችው ዕርምጃ ተገቢ አለመሆኑንና በገሃድ ያለውን እውነት ከግምት የከተተ አይደለም ሲል ቅሬታ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቅሬታውን ከገለጸ በኋላም አሜሪካ ድጋሚ መግለጫን በማውጣት ዜጎቹ ወደ ኢትዮጵያ ቢጓዙ የደህነት ስጋት ሊያጋጥማቸው እንደሚችል በማሳሰብ ላይ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ጉብኝትን የሚያደርጉት ሚኒስትሯ ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ምክክርን የሚያካሄዱ ሲሆን፣ ሃላፊዋ ረቡዕ በጎረቤት ደቡብ ሱዳን ተመሳሳይ ጉብኝት ማድረጋቸው ታውቋል።