(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 6/2010)
በኢትዮጵያ ያለው ግድያና የፖለቲካ ቀውስ በእጅጉ እንዳሳሰባቸው በሐገሪቱ በቅርቡ የተሾሙት የአሜሪካ አምባሳደር ገለጹ።
አምባሳደር ማይክል ሬይነር የመከላከያ ሃይል የሕዝብን ሕይወት መጠበቅ እንጂ በሰልፈኞች ላይ ተኩስ መክፈት የለበትም ሲሉም አሳስበዋል።
አምባሳደሩ እንዳሉት በኢትዮጵያ ያለውን ችግር ለመፍታት ሁሉም የበኩሉን አስተዋጾ ማድረግ ይጠበቅበታል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር በአዲስ አበባ ከተሾሙ ገና 4 ወር ተኩል ጊዜ ብቻ ነው።
እናም በዚህ የአጭር ጊዜ ቆይታቸው በኢትዮጵያ እየሆነ ያለው ጉዳይ በእጅጉ እንዳሳሰባቸው በኤምባሲው የፌስቡክ ገጽ ላይ ገልጸዋል።
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ፣የዲሞክራሲ ተሃድሶ እንዲኖር እንዲሁም ሁሉን አቀፍና አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ ውይይት እንዲኖር ትፈልጋለች።
ይህም ሆኖ ግን ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በኢትዮጵያ በርካታ ተግዳሮቶች እየታዩ መሆናቸውን አምባሳደሩ ገልጸዋል።
የእኔም ሆነ የአሜሪካ ኤምባሲ ሚና ኢትዮጵያ ወደ ጥሩ አቅጣጫ እንድትሄድ መሻት ቢሆንም በሃገሪቱ ያለው ሁኔታ ግን አሳሳቢ መሆኑን መግለጽ እፈልጋለሁ ብለዋልበአዲስ አበባ የአሜሪካው አምባሳደር ማይክል ሬይነር።
አምባሳደሩ እንዳሉት ሕዝቡ በሰላማዊ መንገድ ሃሳቡን ለመግለጽ ሲሞክር በመከላከያ አባላት መገደሉ አግባብ አይደለም።
እናም የመንግስት ታጣቂዎች የሕዝብን ደህንነት ከመጠበቅ ይልቅ በሰላማዊ ሰዎች ላይ መተኮስ ሊያቆሙ ይገባል ነው ያሉት።
እናም ለችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል ባይ ናቸው አምባሳደሩ።
ተቋማትንና ንብረትን ማውደም ተገቢ እንዳልሆነም ነው የገለጹት።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው በቅርቡ የተሾሙት አምባሳደር ማይክል በመልዕክታቸው ያሰመሩበት ሌላው ትልቅ ጉዳይ ለችግትሮች መፍትሄ ለመስጠት ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት የሚል ነው።
በሃገሪቱ የተጀመረውን የተሃድሶ ርምጃ ማስቀጠል ሲገባ ሰውን መግደልና ሕዝብን ማሸበር ሀገሪቱን እንደማይጠቅም በኢትዮጵያ የአሜሪካው አምባሳደር ማይክል ሬይነር አሳስበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተጠራውን ተቃውሞ መነሻ በማድረግ የጥንቃቄ መግለጫ ማውጣቱ ታውቋል።